ለእንስሳት ጤና ትኩረት መስጠት ለሁለንተናዊ የኅብረተሰብ ጤና ማሰብ ነው።

27

ባሕር ዳር፦ ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ሕክምና ሳይንስ ትምህርት ክፍል “የእንስሳት ሕክምና ትምህርትን ማሳደግ እና የአንድ ጤና ትግበራ” በሚል ርዕስ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ቤትም በይፋ ተመሥርቷል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ተወካይ ዲን ሃብታሙ ጣሰው (ዶ.ር) ለሰው ልጅ የጤና መጓደል ምክንያት ከኾኑ ችግሮች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ መነሻ ምንጫቸው ከእንስሳት ነው ብለዋል፡፡ የእንስሳት ሕክምና ላይ ትኩረት ማድረግ ደግሞ የኅብረተሰብ ጤናን መጠበቅ መኾኑን ገልጸዋል።

ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር የሰው ሕክምና፣ የእንስሳት ሕክምና እና የአካባቢ ጥበቃን በአንድ የጤና መርሕ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲውም በአካባቢው የእንስሳት ሃብት ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የትምህርት ክፍሉን ወደ ትምህርት ቤት ማሳደጉን ነው የገለጹት። ትምህርት ቤቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ከመማር ማስተማር ባለፈ በምርምር እና የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በመስጠት የድርሻውን እንደሚወጣ ያስችለዋል ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ገዳም ማንደፍሮ የአማራ ክልል ያለውን የእንስሳት ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል የጥናትና ምርምር፣ የቅድመ በሽታ መከላከል እና የበሽታ ቁጥጥር ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ብቁ የኾኑ የእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የሚያስችል የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ቤት መክፈት አስፈልጓል። በቀጣይ በምርምር በመታገዝ በእንስሳት ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲውም ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር 59 ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ጀመሩ።
Next articleየአማራ ክልል መሪዎች የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች እንቅስቃሴን እየተመለከቱ ነው።