በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር 59 ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ጀመሩ።

28

እንጅባራ: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጸጥታ ችግር ምክንያት ተዘግተው የቆዩ 59 መደበኛ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። ከ2015 ዓ.ም መገባደጃ ጀምሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። የጸጥታ ችግሩ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ300 ሺህ በላይ የሚኾኑ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑም አድርጓል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ወንድማገኝ ማኔ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ውድመት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። 31 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲኾን 167 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት። በዚህም ከ415 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት ማስከተሉን ተናግረዋል።

በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች እና በማኅበረሰቡ ጥምረት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመጠገን እና በአዲስ በመገንባት ትምህርት ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑንም ምክትል ኀላፊው አንስተዋል ። በማኅበረሰቡ፣ በጸጥታ አካላት እና በመሪዎች የተቀናጀ ጥረት ተዘግተው ከቆዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 59 የሚኾኑት መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

ትምህርት ዘግይቶ በጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ቀሪ ጊዜን ታሳቢ ያደረገ የትምህርት ጊዜን በመከለስ የትምህርት ይዘቶችን ለመሸፈን ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2017 የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ መገኘት ከነበረባቸው ከ446 ሺህ በላይ ህፃናት ውስጥ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት 33 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደኾኑ ያነሱት ምክትል ኀላፊው ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የማኅበረሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፎችን ለማግኘት የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ፡፡
Next articleለእንስሳት ጤና ትኩረት መስጠት ለሁለንተናዊ የኅብረተሰብ ጤና ማሰብ ነው።