ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፎችን ለማግኘት የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ፡፡

30

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮች የምታገኘውን ድጋፍ እና ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አሥተዳደር አዋጅ ጸድቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ሥብሠባ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አሥተዳደር አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት አዋጁን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ዘላቂ ፈንድ ከማቋቋም አንጻር እና ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ጥሩ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሀገር ውስጥን አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረጉ ድጋፎችን ለማግኘት የሚያስችል አዋጅ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የራሱ በጀት እንዳልነበረው የገለጹት የምክር ቤት አባላቱ በቀጣይ ራሱን ችሎ በልዩ ፈንድ ተደግፎ እንዲቀጥል የሚረዳ እና በርካታ ሥራዎችም በአዋጁ ውጤታማ እንደሚኾኑ አመላክተዋል፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ ለተተከሉ እና ለሚተከሉ ችግኞች ቀጣይነት ባለው መልኩ በተቀናጀ አግባብ መንግሥት የበጀት ድጋፍ እንዲያደርግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮች እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ሰጭ ምንጮች እና ከካርበን ግብይት ሥርዓቶች የምታገኘውን ድጋፍ እና ጥቅም ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው የተገለጸው፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጡረታ ሕጉ ምን ይላል?
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር 59 ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ጀመሩ።