የጡረታ ሕጉ ምን ይላል?

334

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ 1267/2014 እንደሚያትተው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ 60 ዓመት ሲሞላው ጡረታ እንደሚወጣ ያስቀምጣል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ድንጋጌ ላይ በልዩ ኹኔታ 25 ዓመት አገልግሎት እና 55 ዓመት ዕድሜ ላይ ሲኾን የመንግሥት ሠራተኛው ጡረታ እንደሚወጣ እና የምክር ቤት አባል ከኾነ ደግሞ 50 ዓመት ላይ ሊወጣ የሚችልበት ኹኔታ እንዳለ ሕጉ አስቀምጧል፡፡

ለሁሉም ሰው የሚሠራው ግን 60 ዓመት ሲኾነው ጡረታ መውጣት እንዳለበት ነው ሕጉ ያስቀመጠው፡፡ ከ60 ዓመት በላይ ግን በሕግ አግባብ ሊራዘም የሚችልበት ኹኔታ ሊኖር እንደሚችልም ሕጉ ያስረዳል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በተለያዩ ምክንቶች ከ60 ዓመት በላይ እየሠሩ ሲኾን በአዋጁ ላይ እንደተደነገገው ከጡረታ ዕድሜ በላይ የተሰጠ አገልግሎት ለጡረታ ስሌት እንደማያገለግል እና ክፍያ እንደማይሰላበት ነው አዋጁ በግልጽ ያስቀመጠው፡፡

ሠራተኛው በጡረታ በሚገለልበት ወቅት አገልግሎቱ ካልተያዘ የጡረታ መነሻ ጊዜ ወደ ኋላ ሂዶ በሥራ ላይ እያሉ ለሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ የጡረታ አበል እንዲከፈላቸው በተጨማሪ የሚጠይቁበት ኹኔታ ይኖራል። የማኅበራዊ መድኅን ሽፋን የሚያስፈልግበት አንዱ ዜጎች የገቢ መቆራረጥ እንዳያጋጥማቸው በማሰብ እንጅ ተደራራቢ ጥቅም እንዲያገኙ አይደለም፡፡

የጡረታ አበል የሚከፈላቸው ሥራ እና ደመወዝ ከሚያቋርጡበት ወር አንስቶ እንዲኾን ነው አዋጁ ያስቀመጠው፡፡ በዚህ አዋጅ ከተደነገገው የጡረታ ዕድሜ በላይ በመንግሥት ሥራ ላይ ቆይቶ የሚቀርብ የጡረታ አበል መነሻ የሚታሰበው የመንግሥት ሠራተኛው ከመንግሥት ሥራ አቋርጦ የጡረታ አበል ጥያቄ ለፈንዱ ካቀረበበት ቀጥሎ ካለው ወር የመጀመሪያ ቀን አንስቶ እንደኾነ ያሳያል፡፡

የጡረታ ዕድሜ የሚሰላው የመንግሥት ሠራተኛው የመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠር የሞላው ዕድሜ እንደኾነ ሕጉ ያሳያል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች በራሳቸው ፈቃድ በ55 ዕድሜ ይወጡ እና በተለያዩ ስሞች መልሰው ከዛው ከነበሩበት መሥራ ቤት ይቀጠራሉ። ከዚህ አኳያ ሕጉ ቀድሞ በ55 ዕድሜ መውጣት ስለሚፈቅድ ይህን ተጠቅመው የሌሎችን ተቀጣሪዎች ዕድል ሲዘጉ ይታያል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሕጉ ካስቀመጠው ድንጋጌ ውስጥ አንድ ዕድሜው ሳይደርስ የወጣ የመንግሥት ሠራተኛ በዛው ይሠራበት በነበረው መሥሪያ ቤት የሚቀጠር ከኾነ የጡረታ አበሉ እንዲቋረጥ ሕጉ አስቀምጧል፡፡

ሠራተኛውም ኾነ መሥራያ ቤቶች የያዙትን ሕጋዊ ማስረጃ ሲጠየቁ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልኾኑ ወይም የዚህን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጡ ደንብ እና መመሪያዎች ድንጋጌ አፈጻጸም የሚያሰናክል ድርጊት የፈጸሙ እንደኾነ በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ የሚኾኑ እንደኾነ ሕጉ አስቀምጧል፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚጠይቀውን ማስረጃ ሁሉ እንዲያቀርብ አንቀጽ 53 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

አንድ ሰው ከግል መሥራ ቤት ወደ መንግሥት ከመንግሥትም ወደ ግል የሚቀይርበት ኹኔታ ሲፈጠር አገልግልቱ እና መዋጮው ምን ይኾናል የሚለው ሲታይ ከዚህ በፊት መዋጮውን ለመሥራት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ግለሰቡ ሲቀያየር የደመወዙም ኹኔታ ስለሚቀያየር አፈጻጸሙ ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

ጡረታው ከትውልድ የመተላለፉ ኹኔታንም የማይደግፍ ነበረ። ይህም ሰውየው የሚከፈለው ጡረታ ባዋጣው መጠን ልክ አይደለም፤ የሚከፈለው ይህ ቢኾን ኑሮ እንኳን ለቤተሰቡ ሊተላለፍ ቀርቶ ለራሱም አይበቃውም ነበር። ይህ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ እና የወጭ መጋራትን ለማስተካከል እንዲረዳ ተደንግጓል፡፡

የጡረታ መዋጮ ሕጉ ባስቀመጠው መሠረት አሠሪው መሥሪያ ቤት ሕጉ ባስቀመጠው መሠረት በየወሩ ለጡረታ ፈንድ ማስገባት እንደሚኖርበት ሕጉ አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጅ መሥራ ቤቱ የጡረታ መዋጮውን እስከ ሦስት ወር የማያስገባ ከኾነ ከአሠሪው መሥሪያ ቤት የሒሳብ ቁጥር ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ካልኾነም ያለው ንብረት በጨረታ ተሽጦ እንዲከፈል ሕጉ ይደነግጋል፡፡

ዝቅተኛ የጡረታ አበል የሚሠራው እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደኾነም ሕጉ አስቀምጧል። ይህም የኾነው የወቅቱን የኑሮ ኹኔታ ታሳቢ አድርጎ ወይም ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር እስከ አምስት ዓመት የነበረ ሲኾን ዜጎች የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ የሚሻሻልበት ኹኔታ ዝቅ እንዲል ስለመደረጉ ነው ሕጉ ያስቀመጠው፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ጋር ተወያዩ።
Next articleለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፎችን ለማግኘት የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ፡፡