በበጀት ዓመቱ 597 የመንገድ እና ድልድይ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው፡፡

51

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ከአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ እንዲሁም የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) እንደገለጹት በክልሉ ሰፊ መንገዶችን በመገንባት 2 ሺህ 750 ቀበሌዎችን ማስተሳሰር ተችሏል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ 300 ቀበሌዎችን ለማስተሳሰር እየተሠራ ነው። ኀላፊው በ2017 በጀት ዓመት 630 የመንገድ እና ድልድይ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል። ከዚህ ውስጥም 40ዎቹ ድልድዮች መኾናቸውን አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱም 597 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ነው የቢሮ ኀላፊው ያስገነዘቡት። በበጀት ዓመቱም ለመንገድ ግንባታ 6 ቢሊዮን 49 ሚሊዮን 241 ሺህ 382 ብር መመደቡን ዶክተር ጋሻው ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ 17 ሺህ 142 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ታቅዶ ባለፋት አምስት ወራት ውስጥ 5 ሺህ 64 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ጥረት ተደርጓል። ይህም የዕቅዱን ከ100 በላይ መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው።

በግንባታ ሂደቱ የጸጥታ ችግሩ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቸጋሪ ነበር ያሉት ዶክተር ጋሻው የካፒታል ገንዘብም በፍጥነት አለመለቀቁን በውስንነት አንስተዋል።

የመንገድ ግንባታዎች የሚያልፉባቸው አካባቢዎች ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለመኾንም በችግርነት ተነስቷል።

የቋሚ ኮሚቴ አባላትም የመንገድ ቢሮ የሥራ አፈጻጸም ጥሩ መኾኑን ጠቁመው ቢሮው የተመደበለትን ከፍተኛ ገንዘብ በርብርብ ሥራ ላይ ማዋል አለበት ነው ያሉት። ጥገና ላይም ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበበጋ መስኖ ስንዴ 122 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ጋር ተወያዩ።