
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት “ሕዝባዊ ሚሊሻ የሰላም እና የልማት ጠባቂ ኃይል ነው” በሚል መሪ መልዕክት ለአዲስ ሚሊሻ አባላት ሥልጠና መስጠት ጀምሯል ። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ሚሊሻ የከተማችን የሰላም ዘብ፣ የሕዝባችን ጠባቂ፣ የልማት እና የእድገት ሚናው ላቅ ያለ ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠና የተሳካ እንዲኾን ከተማ አሥተዳደሩ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞች የሚጠበቀውን ሥነ ምግባር በማሟላት ሥልጠናው ያማረ እና የተሳካ እንዲኾን እንዲያደርጉም አሣሥበዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሱፍ አብዱ የኋላ ታሪካችንን ስንቃኝ ሚሊሻ በበርካታ የጦር ግንባር ላይ በቀዳሚነት ለሀገሩ እና ለወገኑ ደም እና አጥንቱን የገበረ ነው ብለዋል፡፡

ከኦሮሞ ብሔረሰሰብ አሥተዳደር ኮሙዩንኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሚሊሻ ለሀገሩ ሕይወቱን የሰጠ ጀግና ሀገር ወዳድ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሠልጣኞች ሥልጠናውን በፍጹም ሀገራዊ ፍቅር እና አንድነት በተሞላበት ስሜት በመውሰድ አርዓያ የኾነ የሰላም አስጠባቂ ኃይል እንዲኾኑም አሣሥበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
