
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከሰላማዊ አማራጮች ጎን ለጎን ደግሞ የሕግ ማስከበር ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በየአካባቢው የሚሊሻ አባት ሥልጠና እየተካሄደ ነው፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝነት ያላቸው ሚሊሻ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የሚኖራቸው ሚና ላቅ ያለ እንደኾነ ይገለጻል፡፡ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ገደቤ ኃይሉ በክልሉ ያለው ሰላም አሥከባሪ እና የሚሊሻ ኃይል ክልሉ የገጠመውን ቀውስ ለመመከት እና ሰላምን ለማስፈን የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ሚሊሻ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከአድማ መከላከል እና ከፖሊስ ጋር በመኾን የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው ነገር ግን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና በሁሉም አካባቢዎች የተሟላ ሰላም እንዲኖር ለማድረግ ሚሊሻ ማሠልጠን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የሚሰጠው ሥልጠና የጸጥታ ኃይሉን የመፈጸም አቅም ከፍ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡ በወረዳዎች እና በቀበሌዎች ላይ ለሚሊሻ ሥልጠና እየሰጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የሚሊሻ ኃይሉ ደከመኝ ሳይል ለክልሉ ሰላም ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ የክልሉን የጸጥታ ችግር በራስ አቅም ለመፍታት እና የሚሊሻ ኃይሉ አቅም እየጎለበተ እንዲሄድ ሥልጠናዎች ወሳኝ መኾናቸውን ነው ያመላከቱት፡፡ እየተሰጠው ያለው ሥልጠና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የሚሊሺያ ኃይሉ ከፍተኛ መነሳሳት ላይ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያለው ጽንፈኛ ኃይል በሚፈጽማቸው ተግባራት እየተጋለጠ እና ሕዝብን እያማረረ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ጽንፈኛው ኃይል ማኅበረሰቡን እንደሚዘርፍ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ ጽንፈኛው ኃይል የሚፈጽመው ድርጊት ከሕዝብ አብራክ የወጣ የማይመስል፣ የባዕዳን ወራሪዎች እንደሚፈጽሙት አይነት እና ከዚያ ያለፈ መኾኑን አንስተዋል፡፡ እየሠለጠነ ያለው የሚሊሺያ ኃይልም የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እና ማኅበረሰቡ ሰላም እንዲያገኝ እንደሚያደርግ ነው ያመላከቱት፡፡
እየፈጸመ ያለው እኩይ ተግባር ሕዝቡን ማስቆጣቱን እና የሚሊሻ ኃይሉም ለሰላም በወኔ እና በእልህ እንዲነሳ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ ሚሊሻ ችግሮችን ተቋቁሞ ለሕዝብ ሰላም የቆመ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ እየተሰጠው ባለው ግዳጅ እና ተልዕኮ እርምጃ እየወሰደ የክልሉን ሰላም እያረጋገጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የማድረግ አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አመላክተዋል፡፡
ለሚሊሻ የሚሰጠው ሥልጠና ከሕዝብ ጋር እየተቀናጀ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ ሕዝብን ይዞ የክልሉን ሰላም እንደሚያረጋግጥም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብሮ ለሕዝብ ሲል መስዋዕትነት የሚከፍል መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል በተፈጥሮ የታደለ፣ በቀላሉ መልማት የሚችል እና ታታሪ ሕዝብ ያለበት ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው ጸጋዎችን ለመጠቀም እና ለማልማት ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ያለ ሰላም የሚራመድ ልማት አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ሰላምን ውጤታማ ለማድረግ ሰላምን ማረጋገጥ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር የራሱን ሰላም ማስከበር እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል፡፡
የሕግ ማስከበሩ ሥራ የተሳካ ኾኖ እንዲቀጥል እና የጽንፈኛውን ኃይል እንቅስቃሴ ለማስቆም ከሚሊሻው ጋር በጋራ መሥራት አለበት ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰቡ ጽንፈኛ ኃይሉን በቃችሁ ማለት እና ለጸጥታ ኃይሉ መረጃ መስጠት መቻል አለበት ብለዋል፡፡ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች ማኅበረሰቡ ምሬቱን እየገለጸ መኾኑን እና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በጋራ እንደሚሠራ ማንሳቱን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ባለው ባሕል እና እሴት አማካኝነት ነፍጥን አንስተው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ሰላማዊ አማራጮችን እንዲመርጡ እና ችግሮቻቸውን በሰላም እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ባቀረበው ጥሪ መሠረት በርካታ ኃይሎች እየገቡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ክልሉ በተሟላ አቅም ወደ ልማት እንዲገባ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት። ለሚሊሻዎች እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!