
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኅላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት ፣ የሁለቱ ሀገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት መወያየታቸው ተመላክቷል፡፡ የኢትዮጵያ እና ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በሥልጠና እና ልምድ ልውውጥ አብሮ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ በቅርቡ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች ተሳታፊ የኾኑበት ምክክር እንደነበር ያነሱት አቶ አደም ስምምነቱ ፍሪያማ መኾኑንምም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች በሥልጠና እና በልምድ ልውውጥ መርኃ ግብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የብልፅግና ፓርቲ ፍላጎቱ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መኾኗን ገልጸዋል፡፡ ግንኙነቱ በፓርቲ ለፓርቲም ኾነ በመንግሥታዊ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ መንግሥታቸው እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾኗ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል።
ከብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ልማት እና ሠላምን ለማስፈን በኢትዮጵያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡ ከታጣቂዎች ጋር እየተደረገ ያለው ስምምንት የሚደነቅ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰው የአንካራ ስምምነትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደኾነም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!