የውኃ እና የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መሠረተ ልማትን አቀናጅቶ በመሥራት የማኅበረሰቡን ጤናማ ኑሮ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

26

ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት በክልል እና በከተማው ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተጎብኝቷል። በጉብኝቱ ላይ የፕሮጀክቱን ግንባታ በቀጣይ ወራት ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክት የከተማዋን ዕድገት በሚመጥን መልኩ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በደብረ ብርሃን ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገለት መኾኑን ገልጸዋል።

የውኃ እና የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መሠረተ ልማትን አቀናጅቶ በመሥራት የማኅበረሰቡን ጤናማ ኑሮ ለማሻሻል የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መሠረተ ልማት ከዓለም ባንክ በተገኘ የበጀት ድጋፍ በባሕር ዳር፣ በጎንደር እና ደሴ ከተሞች ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የንፁህ መጠጥ ውኃ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ አጠቃቀምን ማሻሻልም ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- ወንድይፍራ ዘዉዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር እና የሠራተኞችን ችግር በመቅረፍ አበረታች ሥራዎችን ተመልክተናል” የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን በመጭው የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ውጤታማ ለመኾን የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከወኑ ነው።