”ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር እና የሠራተኞችን ችግር በመቅረፍ አበረታች ሥራዎችን ተመልክተናል” የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች

44

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎች ቡድን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የርዕሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራዎችን ምልከታ አድርጓል። በምልከታው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል እየሠራ ያለውን ሥራ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ለዳኞች ሥልጠና እና የተሞክሮ ልውውጥ መድረጉን፣ የችሎት ቦታዎችን ምቹ ለማድረግ መሠራቱን እና ዲጂታላይዜሽንን ለመተግበር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተወስተዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሥራ እንቅስቃሴ እና ማሻሻያዎች በቋሚ ኮሚቴዎች ተደንቀዋል። የማሻሻያ ንቅናቄውን አብዛኛው ሕዝብ ወደ ሚገለገልባቸው ወረዳ እና ዞኖች ለማውረድም ትኩረት እንዲሰጥ፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በቋሚ ኮሚቴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ተቀብለን የሥራችን ግብዓት እናደርጋለን ብለዋል። ፍርድ ቤቶች ላይ የሚደረግ ማሻሻያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አንስተዋል።

የዳኝነት ነጻነት እንዲከበር፣ ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ፈጣን፣ ግልጽ እና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የዳኝነት ሥርዓት ለማስፈን ምክር ቤቱ እንዲያግዝ፣ የግጭት መፍቻ አማራጭ ሥርዓቶችን ማቋቋም እና ማጠናከር እንደሚገባ፣ ለመልሶ ግንባታው እና ማደራጀቱ እንዲሁም ለመደበኛ ሥራው የበጀት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ዓለምአንተ ያነሱት። በወረዳ እና ዞን የማሻሻያ ሥራው ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል።

ሌላኛው ምልከታ የተደረገበት የርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት የለውጥ ሥራዎች ናቸው። የሥራ ከባቢን ለሠራተኞች እና ለተገልጋዮች ምቹ ለማድረግ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዲጂታላይዜሽንን ለመተግበር የተሠሩ ሥራዎች በምልከታው እና በውይይቱ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በመስክ ምልከታውም አርዓያነት ያለው ሥራ መሠራቱ ተወስቷል። የሠራተኞች ምግብ ቤት እና የሕጻናት ማቆያ መኖሩም የምቹ ሁኔታ ማሳያነት ነው በሚል ተነስተዋል።

ለሠራተኞች ከፊርማ ይልቅ በአሻራ እና መሰል ቴክኖሎጂ ቢኾን፣ የውበት ዛፎች እንዲኖሩ እና በግቢው አትክልት የሚለማበት እንዲኾን አስተያየት ተሰጥቷል። የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላቴ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር እና ለሠራተኞች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል አበረታች ሥራዎችን ማየታቸውን ገልጸዋል። የፍርድ ቤቶችን ሪፎርም ለመተግበር፣ ሠራተኞቻቸው እንዳይቸገሩ ለማድረግ ካፊቴሪያ እንዲኖር በማድረግ፣ የሕጻናት ማቆያ፣ ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ የተሠራው ሥራ አበረታች ነው ብለዋል።

ከተገልጋዮች እና ከኅብረተሰቡ ጋር ለመገናኘት እና መረጃ ለማድረስ የተጀመረው አሠራርም ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል። ለሌሎች ተቋማትም ሞዴል የሚኾኑ ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የሁለቱም ተቋማት ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠር በኩል አበረታች ሥራ እየሠሩ መኾኑን አይተናል ብለዋል።

ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት እና ተቋማት ለሠራተኞቻቸው የኑሮ ውድነትን የሚቀርፉ ሥራዎችን በመሥራት ሠራተኞች በተነሳሽነት እንዲሠሩ ለማድረግ የሚሠራው ሥራም አበረታች መኾኑን ገልጸዋል። የርዕሰ መሥተዳድር የሕጻናት ማቆያ አርዓያነት ያለው ነው። ባየነው ነገር ደስተኞች ነን። እንደ ምክር ቤትም የክትትል እና ቁጥጥር ሥራችን አጠናክረን እንቀጥላለን። የዳኝነት ነጻነት እንዲጠናከር እና ለተነሱ ሌሎች ጥያቄዎች መመለስ ምክር ቤቱ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ዶክተር ደሴ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአፈር አሲዳማነትን የመከላከሉ ሥራ በዕውቀት መመራት አለበት” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleየውኃ እና የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መሠረተ ልማትን አቀናጅቶ በመሥራት የማኅበረሰቡን ጤናማ ኑሮ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡