
ደሴ: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰብል ምርት እና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት አንዱ ነው። በኢትዮጵያ በአሲዳማነት የተሸፈነ የእርሻ መሬት ከ16 ሚሊዮን በላይ ሄክታር ይሸፍናል። እንደ አማራ ክልል ደግሞ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በአሲዳማነት እንደተጠቃ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የአሲዳማ አፈር ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየኾነ በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተቀመጠለት እና ትኩረት ካልተሠጠው በምርት እና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። የአፈር አሲዳማነት ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ያስችላል የተባለለት ዐውደ ጥናት በኮምቦልቻ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ.ር) የመድረኩን ዓላማ በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት “በአሲዳማነት የተጠቃ አፈርን እንዴት ማከም እንዳለብን ለመምከር እና በያገባኛል መንፈስ ወደ ሥራ እንድንገባ ዓላማ አድርገን ለመምከር ነው የተሠባሠብነው” ብለዋል።
ግብርና የኢኮኖሚያችን ዋልታ ቢኾንም በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በርካቶች የምግብ ዋስትናቸውን እንዳያረጋግጡ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት አንዱ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የእርሻ መሬት ደጋግሞ ከመታረሱ ጋር ተያይዞ በአሲዳማነት የተጠቃው መሬት ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።
አሲዳማነትን በመከላከል ደረጃ የተከናወኑ ሥራዎች መኖራቸውን ያመላከቱት ዶክተር ድረስ የተሠሩት ተግባራት በቂ እና በአሳሳቢነቱ ደረጃ ልክ ባለመኾናቸው የአፈር አሲዳማነትን የመከላከሉ ሥራ በዕውቀት መመራት ይኖርበታል ብለዋል። በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ደግሞ የአፈር አሲዳማነትን በመከላከሉ ሂደት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
“በአሲዳማነት የተጠቃን አፈር የተለያዩ ዘዴዎችን በመተግበር አምራችነቱን መመለስ ካልተቻለ በክልሉም ኾነ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል። የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል በኖራ ማከምን ጨምሮ ሌሎች ዘዴዎችን መተግበር እንደሚገባም ጠቁመዋል። የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአሲዳማነት የተጠቃ አፈርን ማከም በሚቻልበት ኺኔታ ላይ ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ለመቀየር ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ተጠይቋል።
በዐውደ ጥናቱ በሀገር ውጥ የተደረጉ ጥናታዊ ጹሑፎች እና በብራዚል የአፈር አሲዳማነትን ለማከም የተከናወኑ ተግባራት ላይ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡ ዐውደ ጥናቱ በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ በግብርና ቢሮ እና በቻምፒዎን ፎር ፉድ ሰኪውሪቲ አክቲቪቲ አዘጋጅነት በተዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የፋብሪካ ባለቤቶች እና መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል።
ዘጋቢ:- ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!