
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቅምባባ ቀበሌ ነዋሪ የሁለተኛ ደረጃ እና የቅምባባ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ባለመጀመራቸው ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። ልጆቼ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው እንዲማሩ ቢጠይቁኝም በአቅም ማነስ ፍላጎታቸውን ማሟላት አልቻልሁም የሚሉት አስተያየት ሰጪው መንግሥት ልጆች የሚማሩበትን አማራጭ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።
በቅምባባ ቀበሌ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ልጆቻችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ እና እንድናስተምር ፍላጎታችን ነው ብለዋል። ነዋሪነታቸው በአልኋይ ቀበሌ ኾኖ ዘመድ ለመጠየቅ ቅምባባ ቀበሌ ያገኘናቸው ወላጅ ትምህርት ቤት ባለመከፈቱ ልጆቻቸው አልባሌ ቦታ መዋል መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪው ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት በተዘጋባቸው ሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ያለዕድሜ’ቸው እየዳሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል። “እኛም ሳንፈልግ በኹኔታዎች አስገዳጅነት የእነሱን መንገድ እንዳንከተል ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱልን ይገባል” ነው ያሉት። የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ተወካይ ዋና አሥተዳዳሪ ጋርዳቸው መኩሪያ በጸጥታ ችግር ምክንያት በወረዳው አሁን ትምህርት እየተሰጠ የሚገኘው በሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው ብለዋል።
ያልተማረ ዜጋን ይዞ ሀገርን ማሳደግ እና መለወጥ አይቻልም ያሉት ተወካይ አሥተዳዳሪው ሁሉም ማኅበረሰብ አካባቢው ሰላም እንዲኾን በርብርብ በመሥራት የተቋረጠውን ትምህርት ማስጀመር ይገባል ብለዋል። በነሐሴ 2017 ዓ.ም ወረዳው ባዘጋጀው የትምህርት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ እንደተገለጸው በ66 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 58 ሺህ 290 ተማሪዎችን እንዲኹም በአምስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 6 ሺህ 940 ተማሪዎችን ለማስተማር እቅዶ ተይዞ እንደነበር አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!