የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት በጋራ ለመሥራት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ያላቸውን ቁርጠኝነት ገለጹ።

48

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጡትን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ተቀብለዋል። ፕሬዝዳንቱ በ2011 ዓመተ ምህረት በነበራቸው ጉብኝት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእድሳት ሥራ ድጋፍ እንደሚሰጡ አሳውቀው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በታደሰው ብሔራዊ ቤተመንግሥት ፕሬዝዳንቱን የተቀበሉ ሲሆን ቤተመንግሥቱንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይ ለብዙ ዘመናት ተዘንግቶ ለቆየው የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ላደረገችው የእድሳት ድጋፍ አመሥግነዋል። ፕሬዝዳንት ማክሮን በበኩላቸው አስደማሚውን የቤተመንግሥት እድሳት አድንቀው በአድዋ መታሰቢያ ግንባታ እንደታየው የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባሕል ለማክበር የተደረገውን ጥረት ክብር ሰጥተዋል።

መሪዎቹ ሰፊ መጠነ ርዕይ ባላቸው የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በኢንቬስትመንት፣ ባሕል እና ትምህርት ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል። የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተም ረጅም ዘመን ለቆየው መሻት ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት ሁለቱ ወገኖች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የነበራቸውን ውሎ የጋራ ፍላጎታቸውን የትብብር ቁልፍ ጉዳዮች የተመለከተ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ማጠናቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ላጠናቀቁት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሽኝት አድርገዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፈረንሣይ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች” ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን
Next article“ልጆቻችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሱ” የተማሪ ወላጆች