አረጋዊያንን በዘላቂነት መደገፍ የሁሉም አካል ልምድ ሊኾን ይገባል።

32

ደሴ : ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የደቡብ ወሎ እና የደሴ ከተማ አሥተዳደር በጋራ ለሚያስገነቡት ሁለገብ የአረጋውያን ገቢ ማስገኛ ሕንፃ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው፣ በተለያየ ደረጃ ያሉ የሥራ ኀላፊዎች፣ባለሃብቶች፣ ባለድርሻ አካላት እና አረጋውያን ተገኝተዋል። አረጋውያኑ የትናንት አርበኞች እና የሀገር ባለውለታዎች ስለኾኑ ለዛሬ እኛነታችን መሠረቶች ናቸው። የሀገርን ባለውለታዎች መንከባከብ፣ ከልምድ እና ከዕውቀታቸው መጠቀም ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።

ሁለገብ ገቢ ማስገኛ ሕንፃው በደሴ ከተማ በተለምዶ ቧንቧ ውኃ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባ ሲሆን ግንባታው 94 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ እና ባለ 8 ወለል መኾኑ በገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል። የሕንጻ ግንባታው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ታምሩ ካሳ አረጋውያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉባቸው ብለዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ቋሚ ገቢ የሚያስገኘው ሁለገብ ሕንፃ አስተዋጽዖው ከፍተኛ እንደሚኾንም በምክክር መድረኩ ተነስቷል።

የንግዱን ማኅበረሰብ በመወከል የተገኙት አቶ አሕመድ ኑሩ “አረጋውያን የሀገር ባለውለታ ናቸው፤ እነሱን ለመደገፍ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ። ያለ ማንም ቀስቃሽ ሁላችንም አንድ ጠጠር ብንጥል ይህን ሕንጻ እናቆመዋለን በመኾኑም የደሴ ህዝብ ድጋፉን እንዲያደርግም እንጠይቃለን ነው ያሉት።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ምሳዬ ከድር ደሴ ከተማ ለሕንፃ ግንባታው መሬቱን ከማመቻቸት ጀምሮ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን አስታውቀዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ቤተልሔም ብርሃኑ በአጠቃላይ ከ25ሺ በላይ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን መኖራቸውን ገልጸው፤ እስካሁን የተለያዩ አካላትን በማስተባበር እና ጊዜያዊ ድጋፍ እየተደረገ መቆየቱን አንስተዋል።

የሕንጻ ግንባታው በ2009 ዓ.ም ቢጀመርም በተለያዩ ችግሮች መዘግየቱን አስታውሰው አሁን ላይ እንደ አዲስ ከሃምሌ ጀምሮ ኮሚቴ በማዋቀር እና የገቢ ማስገኛ ንቅናቄዎችን በመፍጠር ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የቦርዱ ሰብሳቢ ሽመልስ ጌታቸው 712 ካሬ ሜትር ቦታን ለግንባታው ከሶስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ግንባታውን በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንዲሠራ የደሴ ከተማ አሥተዳደር እና የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር መጣመራቸው እና በየደረጃው ሥራውን የሚያሳልጡ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት። ትልቁ የፋይናንስ ዓቅም ማኅበረሰቡ በመኾኑ ተገቢው ድጋፍ ከኅብረተሰቡ ይጠበቃልም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ሙሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰው ልጆች ንግግርም ይሁን ተግባር ሰላም ሊሆን ይገባል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት አባቶች
Next article“ፈረንሣይ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች” ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን