
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሠለጠኑ ሚሊሻዎች ተመርቀዋል፡፡ ሠልጣኝ ሚሊሻዎች በጎንደርና አካባቢው ያለውን የሰላም እጦት ወደነበረበት ለመመለስ ያስችላሉ ነው የተባለው፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አግየ ታደሰ በጎንደር ከተማ እገታ እና የዘረፋ ተግባሮች ይፈጸሙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሚሊሻዎች ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በከፈሉት መስዋዕትነት በከተማዋ መረጋጋት መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ለማስቀጠል ያለመ የሥልጠና ሂደት ሲሰጡ መቆየታቸውንም አመላክተዋል፡፡
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሥልጠና ማዕከል አሠልጣኝ ሻለቃ ፈለቀ ስዩም የዕዙ ማሠልጠኛ ማዕከል ሠልጣኞችን በማሠልጠን በኩል ኀላፊነት መውሰዱን ገልጸዋል።
የክልሉ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ካሁን ቀደም የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጡ እንደነበር የገለጹት ሻለቃ ፈለቀ የአሁኑ ቁርጠኝነት እና ፍቃደኝነት የሚታይበት ነው ብለዋል። አማራ ክልልም ይሁን ጎንደር ከተማ ሰላም እንዲኾን ካስፈለገ ማኅበረሰቡ ከጸጥታ አካሉ ጎን ሊኾን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በሥልጠናው ሲሳተፉ የቆዩ የሚሊሻ አባላት የማኅበረሰቡ የሰላም እጦት ወደ ሥልጠና ማዕከላት ገብተው ሥልጠና እንዲወስዱ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል። በጎንደርና አካባቢው የሚፈጸመው የእገታ እና አፈና ወንጀል ማኅበረሰቡ ችግር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ ሠልጣኞቹ የዘረፋና የእገታ ወኝጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠና መውሰዳቸውንም ገልጸዋል።
በጎንደርም ይሁን በክልሉ ያሉ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ ሰላምን ለማስጠበቅ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!