በስንዴ ለመሸፈን ከታቀደው ማሳ ውስጥ 75 በመቶ የሚኾነውን ማልማት መቻሉን የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።

38

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ በ2017 ዓ.ም የመስኖ ሥራ አፈጻጸም እና የፍራፍሬ እና የቡና ችግኝ ዝግጅት ላይ ከዞኑ ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የመምሪያው ምክትል ኀላፊ መልካሙ አለኸኝ እንዳሉት በ2017 ዓ.ም በዞኑ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው 27 ሺህ 769 ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ አሁን 24 ሺህ 156 ሄክታር ታርሷል። 21 ሺህ 127 ሄክታሩ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል።

አጠቃላይ በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 19 ሺህ 500 ሄክታሩ በስንዴ የሚሸፈን ነው። እስከ አሁን በስንዴ ለማልማት ከታቀደው 75 በመቶ የሚኾነው በዘር ተሸፍኗል። ደቡብ አቸፈር፣ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ይልማና ዴንሳ እንዲሁም ሰሜን አቸፈር የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸውም ገልጸዋል።

እስከ ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም በስንዴ ያልተሸፈኑ ማሳዎችን ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በዞኑ በመስኖ ልማት የታቀደውን ለማሳካት ከ10 ሺህ በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። 58 ዘመናዊ የመስኖ ግንባታዎች፣ ከ2ሺህ በላይ ባሕላዊ የወንዝ እና የምንጭ የመሥኖ አውታሮችን ወደ ሥራ በማሥገባት እየተሠራ ይገኛል።

ከ32 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መመደቡንም ገልጸዋል።

በዞኑ ከመስኖ ልማት 1 ሚሊዮን 368 ሺህ 372 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውስጥ 780 ሺህ ኩንታሉ ከስንዴ ልማት የሚጠበቅ ነው።

በልማቱ ከ89 ሺህ 200 በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ። ዞኑ እንደ አባይ እና ጣና የመሳሰሉ ውኃማ አካላት እና ለመሥኖ ልማቱ ምቹ የኾነ የሚታረስ መሬት ያለው ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኅላፊ አጀበ ስንሻው እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት እየተሠራ ነው፡፡

እስካሁን 78 ሺህ 266 ሄክታር መሬት በስንዴ ተሸፍኗል። ቀሪ መሬቱን ደግሞ እስከ ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም በዘር የሚሸፈን ይኾናል።

የታቀደውን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል 254 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ እየለማ ነው።
Next articleየጎንደር ከተማን ሰላም የተረጋጋ ለማድረግ ቁርጠኛ መኾናቸውን ሠልጣኝ የሚሊሻ አባላት ተናገሩ።