በአማራ ክልል 254 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ እየለማ ነው።

30

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በ2016 የምርት ዘመን 151 ሺህ 625 ሄክታር መሬት በማልማት 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት እንደቻለ የግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አምሳሉ ጎባው ገልጸዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

በ2017 የምርት ዘመን በክልሉ 245 ሺህ 538 አባወራዎች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተሳታፊ እንደኾኑም ነው የገለጹት፡፡

እስካሁን ባለው የምርት ሂደትም 78 ሺህ 266 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል ያሉት ኀላፊው ይህም የዕቅዱ 42 በመቶ እንደኾነ ተናግረዋል።

ቀሪው መሬት ደግሞ እስከ ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም ድረስ ተዘርቶ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።

በዚህም በሁሉም ዞን እና ወረዳ ያሉ መሪዎች እና ባለሙያዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በዘመቻ በመገኘት የልማት ሥራውን እያገዙ ነው ብለዋል።

የስንዴ ልማት ከተረጅነት እና ከድህነት አስተሳሰብ የሚያወጣ በመኾኑ በምርት ሥራው ላይ የሚሳተፉት አርሶ አደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል።

አቶ አምሳሉ ልማቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ላቅ ያለ በመኾኑ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት በንቅናቄ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት ጊዚያቶች አርሶ አደሮች ቴክኖሎጅን እና የተሻሻሉ አሠራሮችን ተቀብሎ ወደ ሥራ የመግባት ልምዱ አነስተኛ እንደነበር ያወሱት አቶ አምሳሉ አሁን ግን ከዚህ አስተሳሰብ በመውጣት በመስኖ ስንዴ ልማት በመሳተፍ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የመስኖ ስንዴ ምርታማነቱን ለማሳደግ የተሻሻሉ አሠራሮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

አቶ አምሳሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞችን እና የከርሰ ምድር ውኃን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውኃ መሳቢያ ሞተሮች እና ለእርሻ ተግባር የሚውሉ ትራክተሮች ለመሥኖ ስንዴ ልማት ሥራ ጥቅም እየዋሉ መኾኑንም ገልጸዋል።

መንግሥት የመሥኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ እንዲኾን ግብዓቶችን ለተጠቃሚው አርሶ አደር በወቅቱ እያደረሰ ይገኛል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሕገወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች ጣልቃ በመግባት በስርጭቱ ላይ እጥረት እንዲከሰት እያደረጉ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት። ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ሕገወጦችን ሊታገላቸው ይገባል ብለዋል።

የመሥኖ ስንዴ ልማት የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አምሳሉ ልማቱ በግብርና ተቋማት ብቻ የሚተገበር ባለመኾኑ መንግሥታዊም ኾነ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ጥናቶች ለተግባራዊ የቱሪዝም ልማት ወሳኝ ናቸው ” አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleበስንዴ ለመሸፈን ከታቀደው ማሳ ውስጥ 75 በመቶ የሚኾነውን ማልማት መቻሉን የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።