”ጥናቶች ለተግባራዊ የቱሪዝም ልማት ወሳኝ ናቸው ” አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

60

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብር የቱሪዝም አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

በአውደ ጥናቱ ወቅታዊ የቱሪዝም ኹኔታዎችን የመቋቋም፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የአጋር አካላት ሚና፣ የዘርፉ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገ ነው።

በአውደ ጥናቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በአውደ ጥናቱ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ቱሪዝም በዓለም ላይ የሚኖረው የምጣኔ ሃብት ድርሻ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። ቱሪዝም ሰላም እንደሚፈልግም አመላክተዋል።

አማራ ክልል ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት ካላቸው ክልሎች አንዱ ነው ያሉት ኀላፊው ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የቱሪዝም ፍሰት እና አቅማችን እየተስተጓጎለ ነው ብለዋል። የቱሪዝም ፍሰቱን ወደ ጥሩ ደረጃ ለመመለስ የቱሪዝም ሰላምን ማስፈን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ቱሪዝም እና ሰላም ተመጋጋቢ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የቱሪዝም ባለድርሻ አካላት በጥናት የሚያቀርቡት መፍትሄ ግብዓት እንደሚኾን ተናግረዋል ። በተለይም ውድመቱ ያስከተለው ማነቆ ምን እንደኾነ በምን መልኩ ቢሠራ ዘርፉ እንደሚነቃቃ መወያየት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአማራ ክልል መንግሥትም የአገልግሎት ዘርፉ እንዲነቃቃ በተለያዩ አማራጮች እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ባለ ድርሻ አካላት በሚያቀርቡት ጥናትና ምርምር የቱሪዝም ጸጋዎችን እና አቅምን በመለየት የማልማት ሥራ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂ ለቱሪዝም ልማት ወሳኝ ግብዓት መኾኑንም ተናግረዋል። ጥናቶች ለተግባራዊ የቱሪዝም ልማት ወሳኝ ናቸው ያሉት ኀላፊው የሚደረጉ ጥናቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት። ምርምሮችን ወደ ውጤት መቀየር እና የባለ ድርሻ አካላትን በማቀናጀት መሥራትን አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል እስካሁን ከ4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሰብል ተሠብሥቧል።
Next articleበአማራ ክልል 254 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ እየለማ ነው።