
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ወራት ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገራት የሥራ ሥምሪት ማድረጋቸውን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች ክብራቸው፣ መብታቸው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሕጋዊ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት ለሥራ የሚሄዱበትን ሥርዓት መዘርጋቱ ይታወሳል፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎችን የሙያ ክህሎት በማስታጠቅ በውጭ ሀገራት የሥራ ሥምሪት ተወዳዳሪ እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው እያደረገው ያለው ሥራ ውጤታማ መኾኑ ተመላክቷል፡፡ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ክህሎት መር የሥራ እድልን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ዜጎች በውጭ ሀገራት መብታቸው፣ ክብራቸው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ እየተደረገ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ የውጭ ሀገር የሥራ ገበያ በማፈላለግ፣ መዳረሻ ሀገራትን በመለየት እና የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈጸም ዜጎች ሕጋዊ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሀገራቱ ያለውን የሥራ ፍላጎት በመለየት ተወዳዳሪ እና ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል። ዜጎች በቅድሚያ የቁጠባ የሂሳብ ደብተር እንዲከፍቱ በማድረግ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በቆጠቡት ገንዘብ ሀብት አፍርተው ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎችም የሥራ እድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል ኹኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ዜጎች የሥራ መታወቂያ እንዲኖራቸው እና በቂ ስሥጠና እንዲያገኙ በማድረግ የግልጸኝነት ሥርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል። ከስድስት ሀገራት እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈጸም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ባለፉት ወራት የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ያደረጉ ዜጎች ቁጥር ከ160ሺህ ማለፉን አመላክተዋል፡፡
ዜጎች መብት እና ደኀንነታቸው እንዲጠበቅ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሥርዓትን ተከትለው ሊሄዱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በደላሎች ተታለው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ማቅናት ከእንግልት እስከ ሕይወት ማጣት የሚያስከትል መኾኑንም ነው ያነሱት፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ዜጎች ራሳቸውን ከአደጋ መጠበቅ አለባቸው ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!