“19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የታለመለትን ዓላማ አሳክቷል” አቶ አገኘሁ ተሻገር

24

ባሕር ዳር:- ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። የታለመለትን ዓላማ ከፍ ባለ ደረጃ አሳክቶ መጠናቀቁንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል፡፡

በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና የሕዝቦችን ትስስር በሚያጠናክር መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል ብለዋል አቶ አገኘሁ። “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት የተከበረው ይህ በዓል ወንድማማችነትን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሠሩ ገልጸዋል።

የዘንድሮው በዓል ካለፉት በዓላት በተለየ ኹኔታ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ደረጃ በሚመጥን መልኩ ከፍ አድርጎ ማክበር የተቻለበት እንደነበርም አስታውሰዋል። በዓሉ የሀገራችንን በጎ ገጽታ መገንባት የተቻለበት ኾኖ አልፏል ያሉት አፈ ጉባኤው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቱባ ባሕላቸውን፣ የዕርስ በዕርስ ግንኙነታቸውን፣ መተሳሰባቸው እና ታሪካቸውን በአደባባይ ለመላው ዓለም ማሳየት የቻሉበት፣ ብዝኀነታችን ውበታችን እና አንድነታችን መኾኑን በግልጽ ያሳየንበት በዓል ነው ብለዋል።

አቶ አገኘሁ የበዓሉን ዓላማ መሠረት በማድረግ የአዘጋጁን ክልል ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ቦታዎች፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ሐብቶች በስፋት ማስተዋወቅ እንደተቻለ ጠቅሰው በዓሉ የክልሉን የኢንቨስትመንት እና የልማት ሥራዎች ለማነቃቃት ትልቅ እድል እንደፈጠረ አመላክተዋል::

በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለደቡብ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ፣ ለሁሉም የጸጥታ እና ደኅንነት አካላት፣ ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች የላቀ ምስጋና አቅርበዋል:: ባንቺ ይርጋ መለሠ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነት እና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አጠቃላይ የበዓሉን አከባበር አስመልከቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ማኔጅመንት እና አሥተባበሪ ኮሚቴ አባላት ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።

19ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አሥተዳደሮች፣ ከሀገር ውጭ ከአስር በላይ በሚኾኑ ኢምባሲዎች እና ቆንስላዎች በድምቀት እንደተከበረ በሪፖርቱ ተጠቅሷል ::

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልማት ሥራዎች ውጤታማ ኾነው እንዲቀጥሉ ድጋፋችንን እንቀጥላለን” አደም ፋራህ
Next articleከ160 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት አድርገዋል፡፡