
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሥተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በአማራ ክልል አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ፊቱን ወደ ልማት ማዞሩን ነው የተናገሩት። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰፋፊ የልማት ሥራዎች በውጤታማነት እየተተገበሩ መመልከታቸውንም ገልጸዋል። በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማት በጥሩ ኹኔታ እየተሠራ መመልከታቸውን ነው የተናገሩት።
የኮሪደር ልማት ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ ያስቻለ መኾኑንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት ከተሞች የተዋቡ እና ለነዋሪዎች የተመቹ እንዲኾኑ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የዜጎችን አኗኗር የሚቀይር፣ ከተሞች ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲኾኑ የሚያደርግ መኾኑንም አመላክተዋል። የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲጨምር እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ስላሉት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። የኮሪደር ልማት በውጤታማነት እንዲቀጥል እንደሚደረግም ተናግረዋል። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እየተገነባ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማዋ ነዋሪዎች እየተሳተፉበት መኾኑንም ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የዜጎችን የኑሮ ኹኔታ የሚያሻሽል የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን መመልከታቸውንም ተናግረዋል።
የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም ገልጸዋል። የሌማት ትሩፋት በውጤታማነት እየተገበሩ ከሚገኙ አካባቢዎች የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አንደኛው መኾኑን ነው የተናገሩት። በሌማት ትሩፋት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መኾኑን ገልጸዋል። በባሕር ዳር ያለው የሌማት ትሩፋት ለከተማዋ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም ተናግረዋል።
በከተማዋ በወተት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በዓሳ ሃብት ልማት እና በሌሎች የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ውጤታማ ሥራዎች አሉ ነው ያሉት። እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ተኪ ምርትን ማምረት እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማምረት የሚቻለው በየአካባቢው ጸጋውን በመጠቀም ነው ብለዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ጸጋዎችን ተጠቅሞ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር ይገባል ነው ያሉት። ብልጽግና ፓርቲ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የተናገሩት አቶ አደም እየተሠራ ባለው ሥራ ለውጥ እየተገኘ ነው ብለዋል። አሁን የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት። ከተረጅነት በመላቀቅ የተሟላ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።
“የልማት ሥራዎች ውጤታማ ኾነው እንዲቀጥሉ ድጋፋችንን እና ክትትላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት። ኅብረተሰቡም እየተተገበሩ ካሉ እና ከተቀረጹ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲኾን ሥራዎችን መደገፍ እና የአካባቢውን ጸጋ መጠቀም አለበት ብለዋል። ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!