
ሰቆጣ: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የወባ ወረርሽኝ ለመግታት የዘመቻ ሥራ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታውቋል። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአንደኛው ሩብ ዓመት የወባ ወረርሽኝ ከነበረበት 42 በመቶ ወደ 52 በመቶ አድጓል። ይህን ለመከላከልም ከ52 ሺህ በላይ ቤቶችን የኬሚካል ርጭት ተካሂዷል። ከ32 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበርን ወባ ለሚከሰትባቸው ወረዳዎች በማከፋፈል ጥረት መደረጉም ታውቋል።
የወባ ወረርሽኝ ከተከሠተ በኋላ ከመታከም ይልቅ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ በማስፈለጉ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በየሳምንቱ አርብ የሚካሄድ” በጠንካራ የአርብ እጆች የወባ ወረርሽኝን እንከላከላለን” በሚል መሪ መልዕክት የንቅናቄ ዘመቻ ማድረግ ከተጀመረ ስምንተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል።
የወባ በሽታ በስፋት ከሚከሰትባቸው ወረዳዎች አንዱ የስሃላ ሰየምት ወረዳ ሲኾን በሽታውን ለመግታትም የመሽሀ ከተማ 01 ቀበሌ እናቶች በ1 ለ 30 አደረጃጀት የወባ ትንኝ መራቢያን ማዳፈን እና ማፋሰስ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ወይዘሮ የሺዓለም ሙላቴ እና ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ ሹሙ ተናግረዋል።
እርጥበታማ ቦታዎችን በማፋሰስ እና የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀማቸው የቤተሰቦቻቸውን ጤንነት መጠበቅ እንደቻሉም ነው የነገሩን። የስሃላ ሰየምት ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ጋሻው ነጋ በወረዳው የነበረው የወባ በሽታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል። በቅድመ መከላከል ዘርፍ ጠንክረን በመሥራታችን በወባ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ቀንሷል ነው ያሉት።
በዋግ ኽምራ ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት ስርጭቱ በሳምንት ከ3 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ተጠቅተው እንደነበር የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ የወባ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ አበበ በለጠ ገልጸዋል። ጠንካራ የአርብ እጆች ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ በእጅጉ መቀነሱን የገለጹት አቶ አበበ ለዚህም የቅድመ መከላከሉ ሥራ ውጤታማ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ዘመቻው እስከ ታኅሣሥ 30 ድረስ የሚቀጥል ሲኾን የወባ ትንኝ በተፈጥሮ ከጥር በኋላ የመራባት አቅሟ እንደሚዳከም ነው ባለሙያው ያብራሩት። በቀጣይም የወባ ወረርሽኝ ከመፈጠሩ አስቀድመን በዘመቻ በመከላከል እና እንዳይጨምር ለማድረግ ጠንካራ የአርብ እጆች ዘመቻ ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበት ነው ተብሏል።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!