
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግፍ የሰለቻቸው አደባባይ ወጥተዋል። መከራ የበዛባቸው በቃን ብለዋል። መገፋት የመረራቸው ተውን እያሉ ጮኸዋል። ልጆቻቸው የሚታገቱባቸው፣ መንገዶች የሚዘጉባቸው፣ የእለት ጉርሳቸው የሚወሰድባቸው የዓመት ልብሳቸው የሚገፈፍባቸው ተውን እያሉ በአደባባይ ውለዋል።
አዎን በቃን፣ አዎን ሰልችቶናል፣ አዎን ግጭት አጉብጦናል፣ መከራ በዝቶብናል፣ አዎን የመከራ ጽዋው ይደፋልን ያሉ ድምጾች ዳር እስከ ዳር ተሰምተዋል። ስሙን፣ ሰላማችን መልሱልን፣ ልጆቻችንን ተውልን፣ አረጋውያን በሰላም ይመርቁን፣ የሃይማኖት አባቶች ያስተምሩን፣ ይገስጹን፣ የሀገር ሽማግሌዎች ያስታርቁን፣ አታግቱን፣ አትዝረፉን፣ አትቀሙን፣ አባቶቻችንን አታዋርዱብን፣ አትግደሉብን፣ የአባቶቻችን ወግና ሥርዓት አትናዱብን፣ ተወልደን ባደግንባት፣ ልጆች ወልደን ወግ ማዕረግ ባየንባት ቀዬ እንዳንኖር አትፍረዱብን እያሉ ወጥተዋል።
ሰላምን የናፈቁ አንደበቶች፣ ግጭትን የጠሉ ልቦች፣ ለሰላም የተዘረጉ እጆች በጎዳናዎች ተመላልሰዋል። በየአደባባዮች ጎልተዋል። የጠፋች ሰላማቸውን በአደባባይ እየፈለጉ ውለዋል። በቃን ያሉ ድምጾች፣ ለሰላም የጮኹ አንደበቶች በርክተዋል። ከፍ ብለው ተሰምተዋል። ጦርነት ይብቃን፣ ሰላም ይምጣልን እያሉ ጎዳናዎችን አጣበዋል።
የሚታገቱት ፣ የሚዘረፉት በርክተዋል፣ በጉልበተኞች ሃብት እና ንብረታቸውን የሚያጡት በዝተዋልና ከእንግዲህስ በቃን ብለዋል። የግፍ ጽዋ መረራቸው። በመከራ ውስጥ መኖር ሰለቻቸውና ተውን ብለው በአደባባይ ውለዋል። እንደ ፈጣሪ የሚከበሩት የሃይማኖት አባቶች ሲገደሉ እያዩ እንዴት አይበቃቸው? ዝናብ ያፈራቸው፣ ሀገር ምድሩ የሚታዘዝላቸው፣ በቀጭን ዘንግ ጥላቻ የሚወድቅላቸው፣ ደም የሚደርቅላቸው የሀገር ሽማግሌዎች ክብራቸው ሲዋረድ፣ በእንብርክክ ሲሄዱ እያዩ ያማቸዋል እንጂ ለምን አያማቸው? ሕጻናት ከእናቶቻቸው ጡት እየተነጠሉ ሲታገቱ እየተመለከቱ ይቆጫቸዋል እንጂ ለምን አይቆጫቸው ? አረጋውያን ሀገር ከሚመርቁበት፣ ትውልድን ከሚያስተምሩበት ጎጆ እየታፈኑ ሲወሰዱ ያንገበግባቸዋል እንጂ ለምን አያንገበግባቸው?
የአማራ አርሶ አደሮች በቀያቸው የደረሰባቸው ግፍ ተነግሮ አያልቅም። በሬዎቻቸውን እነ ወይኖን፣ እነ ዘገርን፣ እነ ደባስን፣ እነ ፈንዛን፣ እነ ደግፍን ሲነዱባቸው፣ እነ ይመርቀንን ከቀንበሩ ፈትተው ሲያርዱባቸው፣ ሞፈር ሲያሰቅሉዋቸው፣ ላሞቻቸውን እነ ቦራን፣ እነ ሻሸልን፣ እነ ዛጎልን፣ ከጥጆቻቸው ነጥለው ሲወስዱባቸው ይበቃቸዋል እንጂ ለምን አይበቃቸውም?
የተስፋ ብርሃን የሚያዩባቸውን ልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታ ሲነጥሉባቸው፣ ከትወልድ ሁሉ ወደ ኋላ ሲያስቀሩባቸው፣ ተቋሞቻቸውን ሲያፈርሱባቸው፣ ወግና ባሕሎቻቸውን ሲያጠፉባቸው፣ ለልጆቻቸው በመሶብ ያስቀመጧትን ጭብጦ ሲነጥቋቸው፣ በጎቻቸውን እና ፍየሎቻቸውን ወስደው ሲጨርሷቸው በቃን ይላሉ እንጂ ለምን አይበቃቸውም?
ከቀን ቀን ለሚያቆረቁዛቸው ጦርነት ሳይወዱ በግድ ቀለብ ሰፋሪ ሲኾኑ ይበሽቃቸዋል እንጂ ለምን አይበሽቃቸውም? ለልጆቻቸው ሳያጎርሱ ተገድደው ሌሎችን ሲያጎርሱ የኖሩት፣ ልጆቻቸውን እያስራቡ ሌሎችን የመገቡት ይበቃቸዋል እንጂ ለምን አይበቃቸውም? በቃን ብለው በጎዳናዎች መሙላታቸው፣ አደባባይ ማስጨነቃቸው፣ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸው፣ ከዚህ በኋላ በሰላማችን የሚመጣብንን እንደ አባታችን ገዳይ እናየዋለን ማለታቸው ይፈረድባቸዋልን? መከራ እኮ ሲበዛ ይገነፍላል፣ ትዕግሥትም እኮ ያልቃል፣ መከራን የተሸከመ ትክሻም እኮ ይዝላል።
” አወይ ልጅ ማሰሪያው አወይ ልጅ ገመዱ ጎጆማ ምን ይላል ጥለውት ቢሄዱ” እያሉ ለልጆቻቸው ሲሉ መከራን የተቀበሉት፣ ጀግኖች ሳሉ ቀን ይለፍ ብለው አንገታቸውን ደፍተው የከረሙት፣ ዘመን ይሽረዋል ብለው በትዕግሥት የጠበቁት፣ ምድሩ ሰው አጥቷልን፣ መካሪ ጠፍቷልን እንባላለን፣ በውስጣችን ይዘን በቀስታ እንፍተው ብለው ዝም ብለው የባጁት አልኾን ሲል በቃን ብለው መውጣታቸው የተገባ አይደለምን? ደግ አደረጉ አያስብልምን? የትልቅ ሕዝብ ልኩ ይህ ነው አያሰኝምን?
ዘመን ያመጣውን ዘመን እስኪወስደው እያሉ የመከራ ጽዋን መጋት እኮ ይሰለቻል። የመከራ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ እኮ በቃን ብሎ መነሳት ይመጣል። በአማራ ክልል የኾነው ይህ ነው። ከአንድ ዓመት በላይ በግጭት ውስጥ ኾኖ የከረመው ሕዝብ በቃን ብሎ ወጥቷል። ሰላማችን መልሱልን እያለ ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቷል። የአማራ ክልል ከተሞች ሰላምን በሚሹ ሰዎች ተሞልተው ውለዋል። ከዳር ዳር ሰላም ሰላም የሚሉ ድምጾች ተስተጋብተዋል። ጦርነት ተወግዟል። ግጭት ተንቋል። በልጆቻቸው ዕድሜ የሚመጣው ሁሉ ተወግዟል።
በአማራ ክልል ሰላምን የናፈቁ ግጭትን የጠሉ እና የጣሉ ሰልፎች በስፋት ተካሂደዋል። በሰልፎችም ሰላም ተሰብኳል። አንድነት ተቀንቅኗል። ፍቅር ተዘምሯል። ጦርነት እና ጥላቻ ይቀር ዘንድ ተለፍፏል። ለችግሮች ሁሉ መፍቻው ውይይት ይኾን ዘንድ ተጠይቋል። ሰልፎቹ እልፍ ትርጉም አላቸው። ሰልፎቹ መፈክር ይዞ ከመውጣት በላይ ናቸው። ድምጽ አሰምቶ ከመመለስ ያልፋሉ። ሰልፎቹ መሬት ላይ ያለውን ዕውነት ይገልጻሉ፣ መፍትሔውን ይጠቁማሉ። የነገውንም ይተነብያሉ። ሰልፎቹ እልፍ መልክ አላቸው። የሕዝብን ምሬት ያሳያሉ። የከረመውን መከራ ይገልጻሉ። ዕውነትን በአደባባይ ይገልጣሉ። የግፉን መጠን ይነግራሉ። ከዚህ በላይ አንታገስም የሚል መልዕክት ይነግራሉና።
ዝም ብሎ የኖረ ፣ ያልፋል ብሎ አንገቱን ደፍቶ አንድ ዓመትን የተሻገረ ሕዝብ ሰላም ይሻላል ጦርነት በቃን ብሎ ሲወጣ ያወቀበት ይድናል። ድምጹን የሰማ መልካም ነገርን ያደርግ ዘንድ ይወዳል። በታሪክ ላይም ስሙን ያጽፋል። ከዳር ዳር የተሰሙትን የሰላም ድምጾች የናቀና የተወ ቢኖር ግን መንገዱ የከበደች፣ ዘመኑም የተጨነቀች ትኾናለች። ስለ ምን ቢሉ ጫካ ለአንበሳ ሞገሱና ግርማው፣ መጠጊና ደጀኑ እንደኾነ ሁሉ ታጋይም ያለ ሕዝብ ምንም ነውና።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!