
ወልድያ: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጸጥታ ችግር ምክንያት አልሚ ምግብ ማድረስ አስቸጋሪ ኾኖ ለቆዩ ወረዳዎች ተደራሽ እያደረገ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል። ባለፉት ወራት በሰሜን ወሎ ዞን ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለህጻናት ወጥ የኾነ አልሚ ምግብ ለማድረግ አስቸግሮ እንደ ነበር የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሃብታሙ አዱኛ ገልጸዋል።
በተለይም በዳውንት እና ቡግና ወረዳዎች ለመድረስ አስቸጋሪ እንደነበር ነው የገለፁት። በኅዳር ወር በተሠራው የሥነ ምግብ ልየታ 2 ሺህ 294 ህጻናት የከፋ የምግብ እጥረት ያለባቸው እና 39 ሺህ 156 ህጻናት ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ የምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት በዞኑ መኖራቸው ታውቋል ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ 49 በመቶ የሚኾኑት በቡግና ወረዳ የሚገኙ ህጻናት መኾናቸውን ገልፀዋል። ከዚህ አኳያ ባለፉት ስድሥት ወራት 7 ሺህ 227 ካርቶን አልሚ ምግብ እና 56 ካርቶን ወተት በዞን ደረጃ ተሰራጭቷል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ ለቡግና ወረዳ 932 ካርቶን አልሚ ምግብ፣ 16 ካርቶን የተለያዩ ብስኩቶች እና ተጨማሪ አልሚ ምግቦች በሁለት ዙር መሰራጨቱን ተናግረዋል።
ፀረ ተኅዋስያን መድኃኒቶችም ለወረዳው መድረሱን ተወካይ ኀላፊው አስረድተዋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት አልሚ ምግቦቹ በጊዜው መድረስ ባለመቻላቸው በምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት ስላሉ እነሱን ለማዳን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ህጻናቱ በአብዛኛው በጤና ኬላ ደረጃ የሚታከሙ ሲኾን በጤና ጣቢያ ደረጃ የሚታከሙ ልጆችም ሕክምናው እየተሰጣቸው ነው።
አልሚ ምግቡን እና መድኃኒቱን ለማድረስ የክልል ጤና ቢሮ፣ ዩኒሴፍ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ከጤና መምሪያው ጋር በትብብር እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!