
ወልድያ: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 -17 የመኸር ወቅት ተመጣጣኝ ዝናብ በመዝነቡ እና ድርቅ ባለመከሰቱ ምክንያት የተረጅዎች ቁጥር ካለፈው ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ መቀነሱን የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለሙ ይመር ከነበርው የአየር ጸባይ ምቹነት ጋር በተያያዘ ለምርት መልካም ስለነበር ባለፈው ዓመት ከነበረው የተረጅዎች ቁጥር ቀንሷል ብለዋል።
ይሁን እና ምርት እስከሚሰበሰብ ድረስ እርዳታ ሊደረግላቸው የሚገባ ወገኖች እንዳሉም ጠቁመዋል። በክልሉ ያለው የፀጥታ ስጋት በአግባቡ እርዳታ ማድረስ አስቸግሮ እንደነበርም አንስተዋል።
መንግሥታዊ ያልኾኑ ረጅ ተቋማት እየወጡ በመኾኑ ለሕዝቡ በፍጥነት ለመድረስ ከመንግሥት የጸጥታ መዋቅር፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ ግብር እና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ምክክር በማድረግ በጥምረት እርዳታው ለሚገባቸው ወገኖች ለማድረስ እየተሠራ ነውም ብለዋል አቶ አለሙ።
ለ110 ሺህ 563 የቡግና ወረዳ ተረጅዎች ብቻ 16 ሺህ 583 ኩንታል ዕህል ከኮምቦልቻ መጋዘን ተጭኖ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ወቅት ድረስ 38 ተሳቢዎች ጉዞ ላይ መኾናቸውም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!