
ወልድያ: ታኅሳስ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016/17 የመኽር ወቅት ተመጣጣኝ ዝናብ ዘንቧል። ተመጣጣኝ ዝናብ መዝነቡ እና ድርቅ ባለመከሰቱ ምክንያት የተረጅዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ይመር ከነበረው የአየር ጸባይ ምቹነት ጋር በተያያዘ ለምርት መልካም ስለነበር ባለፈው ዓመት ከነበረው የተረጅዎች ቁጥር አንጻር 80 በመቶ ቀንሷል ብለዋል።
ይሁንና ምርት እስከሚሰበሰብ ጊዜ ድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ ወገኖች እንዳሉም ጠቁመዋል። በክልሉ ያለው የፀጥታ ስጋት በአግባቡ እርዳታ ማድረስ አስቸግሮ እንደነበርም አንስተዋል።
መንግሥታዊ ያልኾኑ ረጅ ድርጅቶች እየወጡ በመኾኑ ለሕዝቡ በፍጥነት ለመድረስ ከመንግሥት የጸጥታ መዋቅር፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተደርጓል። ምክክሩን ተከትሎም በጥምረት ድጋፉ ለሚገባቸው ወገኖች ለማድረስ እየተሠራ ነውም ብለዋል አቶ ዓለሙ።
ለ110 ሺህ 563 የቡግና ወረዳ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ብቻ 16 ሺህ 583 ኩንታል እህል ከኮምቦልቻ መጋዘን ተጭኖ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!