
ሰቆጣ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የዋግ ኽምራን ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም ያለመ የምክክር መድረክ በሰቆጣ ከተማ ባለፉት ሦስት ቀናት ተካሂዷል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በዓሳ ሃብት፣ በእንሰሳት እርባታ፣ በማር ምርት እና በማዕድን ሃብቶች የበለጸገ ዞን ነው። ጸጋዎቹን በዘመናዊ መንገድ እና በተጠና መልኩ መጠቀም ባለመቻሉ ምክንያት ሕዝቡ መጠቀም ባለባቸው ልክ ሳይጠቀሙ ቆይተዋል። ነገሩን በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ የሚያደርገው ደግሞ የመሠረተ ልማት እጥረት ነው።
የውይይቱ ተሳታፊ የድሃና ወረዳ ነዋሪው አቶ ካሳ ታረቀኝ በእንሰሳት ዘርፍ በወረዳው ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም በዘመናዊ መንገድ ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ እጥረት እንደነበር ጠቁመዋል። በቀጣይም የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ውጤታማ ማኅበራትን በመደገፍ እና ዘመናዊ አሠራሮችን በመከተል መሬት ላይ የሚታይ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ የአብርገሌ ወረዳ እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቀኜ እነተ ወረዳው በወርቅ፣ በበግ እና ፍየል እርባታ፣ በተከዜ ዓሳ እና በለውዝ ምርት የሚታወቅ እንደኾነ ገልጸዋል። በተለይም በዓሳ ምርቱ በርካታ ወጣቶች እየሠሩ ቢኾንም የመረብ እጥረት፣ የመንገድ እና የመብራት መቆራረጦች ወጣቱ ጠንክሮ እንዳይሠራ እንቅፋት ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም የመሠረተ ልማት እጥረቶችን ከአጋር ተቋማት ጋር በመነጋገር ለመፍታት እንሠራለን ያሉት ኀላፊው ወጣቱ ያሉንን ጸጋዎች በአግባቡ ተረድቶ እንዲሠራ እገዛ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል። ጸጋዎቻችን በዘመናዊ አሠራር ለመቀየር የጠነከረ ባለሙያ እንደሚያሥፈልግ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንሰሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አያሌው ገልጸዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶችን በማገዝ በኩል ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም አጠናክሮ ከመቀጠል አኳያ የቤት ሥራችንን ማጠናከር እንደሚገባ ነው ኀላፊው ያሳሰቡት፤ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ካለው 110 ሺህ የንብ ቀፎ ውስጥ 9 በመቶ ሚኾነው በዘመናዊ ቀፎ ያለ መኾኑን ዘርፉ እንዳልዘመነ የሚያመላክት ነው ያሉት አቶ ሳሲይ መንግሥትም የዋግ ኽምራን ጸጋዎች በመለየት የመደገፍ እና ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ እንደሚኾን ነው ያብራሩት።
በዋግ ኽምራ ያሉ የማር፣ የበግ እና ፍየል፣ የዓሳ ሃብትን በማስተዋወቅ በኩል ከአጋዥ ድርጅቶች እና በዘርፉ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን ናቸው።
ጸጋዎችን በመለየት ትልልቅ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም የተጠናከረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለተከታታይ ሦስት ቀናት የተሰጠው የዋግኽምራ ጸጋዎችን በዘመናዊ መንገድ ለመጠቀም ያለመ የውይይት መድረክ ተጠናቅቋል።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!