
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀንን እያከበረ ነው። የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀኑ “ከአደጋ ለጸዳ የወደፊት ሕይዎት ወጣቶችን ለማጠናከር እና ለማብቃት ትምህርት ያለው ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተከበረ የሚገኘው።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስተና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ አደጋዎች መከሰታቸውን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የጎርፍ፣ የድርቅ፣ የበሽታ ወረርሽኝ፣ የአምበጣ መንጋ እና ሌሎች ችግሮች መከሰታቸውን ነው የገለጹት።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይገባልም ነው ያሉት። አደጋን ሊቋቋም የሚችል ዘርፈ ብዙ እና ማኅበረሰብ አቀፍ ስትራቴጂ መንደፍ ብሎም መተግበር እንደሚገባም አመላክተዋል። በየአካባቢው ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል፣ ለመቀነስ እና ተጎጂ ለሚኾኑ ወገኖች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ግልጽ አሠራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
በክልሉ በጸጥታ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች የሚመጡ ችግሮችን መንግሥት ምላሽ እየሰጠባቸው እንደኾነ ነው የገለጹት። የአደጋ መከላከል ሥራ ዘርፈ ብዙ እና በተለያዩ አካላት ተሳትፎ የሚሠራ መኾኑንም ነው ያስረዱት። በተለያዩ ምክንያቶች ተጎጂ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በወቅቱ አስፈላጊ ድጋፍ የማቅረብ እና ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
በክልሉ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሲደርስ መቆየቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተጨማሪ ችግሮችን መፍጠሩን ነው የገለጹት። በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
ፈጣን እና ብቁ የአደጋ ምላሽ ለመስጠት የራስ አቅምን ማሳደግ እና ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
የተጀመረው በምግብ ራስን የመቻል ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የአደጋ ስጋትን ለመከላከል እና ለመቀነስ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይገባል ነው ያሉት። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲፈተን መቆየቱን ተናግረዋል።
አደጋ ከደረሰ በኋላ ለመከላከል የተሠራው ሥራ መልካም እንደኾነ የተናገሩት ኀላፊው ቀድሞ በመከላከል በኩል ክፍተቶች እንደነበሩ ነው ያስረዱት። የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። የቅድመ መከላከል ሥራዎች አደጋ እንዲቀንስ እንደሚያደርጉ እና ሲከሰትም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችሉ ነው ያስገነዘቡት።
በበዓሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!