“አደጋን መከላከል የሚቻለው ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

33

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀንን እያከበረ ነው። የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀኑ “ከአደጋ ለጸዳ የወደፊት ሕይዎት ወጣቶችን ለማጠናከር እና ለማብቃት ትምህርት ያለው ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በበዓሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉን (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በክብረ በዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አደጋ ሁልጊዜ የሚያጋጥም እና ከሰው ልጆች ጋር አብሮ የሚኖር ክስተት ነው ብለዋል። ከሰው ልጆች ሕይዎት ጋር አብሮ የሚቀጥል አደጋን መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።

“አደጋን መከላከል የሚቻለው ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ነው” ብለዋል ምክትል ርእሰ መሥተደድሩ። ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ከተቻለ አደጋው ቢከሰት እንኳ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ነው ያሉት። ዘላቂ ልማት ሲኖር ማኅበራዊ እና ሀገራዊ አቅም ያድጋል ብለዋል።

ማኅበራዊ እና ሀገራዊ አቅም ሲያድግ አደጋን መከላከል እና መቀነስ እንደሚቻል ነው የተናገሩት። የአደጋ አመራር ሥራችን ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረገ መኾኑን አለበት ብለዋል። አደጋ ቢፈጠር እንኳን ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ መኾን መቻል አለበት ነው ያሉት።

የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ አሳሳስበዋል። ቅንጅት እንዳይፈጠር እንቅፋት የሚኾኑ ችግሮችን መፍታት ይጠበቃል ነው ያሉት። ቅንጅታዊ አሠራር ሲኖር አደጋን መከላከል እንደሚቻል እና ሲከሰትም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ነው ያሉት።

በራስ አቅም ችግሮችን ለመመለስ የሚደረገውን ሥራ በቁርጠኝነት መምራት ይጠበቃል ብለዋል። ለአደጋ ምላሽ የሚኾን ሃብት እና ዓቅም ማሰባሰብ ይገባል ነው ያሉት። ለአደጋ ስጋት መነሻ የሚኾኑ የጸጥታ ችግሮችን ቀድሞ መፍታት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የአደጋ ተጋላጭነት የቀነሰ እንዲኾን እና አደጋ ቢከሰት እንኳን በፍጥነት ምላሽ የሚሰጥ ክልል እንዲኾን እንሠራለን ብለዋል። የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ እና ለመከላከል በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት እየተሠራ መኾኑን በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ወረዳ አስታወቀ።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት፦