
ደባርቅ: ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የቱሪዝም መስክ ለማነቃቃት ያለመ መድረክ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት ተካሂዷል። በመድረኩ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ ተዳክሞ ቆይቷል። ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ያለመ መድረክ በደባርቅ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደባርቅ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሰለሞን ጌትነት ቱሪዝም እና ሰላም የማይነጣጠሉ እና ተደጋጋፊ መኾናቸውን አንስተዋል። መስኩን ለማነቃቃትም እየተካሄዱ ያሉ መድረኮች ወሳኝነት አላቸው ብለዋል።
የደባርቅ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታው ቢረሳው ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ዛሬ የተካሄደው መድረክም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል። የቱሪዝም ዘርፉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አቅፎ የያዘና የብዙ ሰው እንጀራ ነው ያሉት ኀላፊው ዘርፉን ማነቃቃት ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ያስችላል ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ ሲሳተፉ አሚኮ ያነጋገራቸው መምህር ብዙነህ ካሴ ቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚፈልግ ዘርፍ በመኾኑ አብዝቶ ሰላምን ይፈልጋል ብለዋል። ሰላም ከሌለ ቱሪዝም እንደማይኖርም አስረድተዋል። መምህር ብዙነህ የቱሪስት ፍሰቱ በመቀዛቀዙ ምክንያት በርካታ ሰዎች ለሥራ አጥነት እንደተዳረጉም ነው የገለጹት።
መምህር ይሄይስ ጀጃው በዞኑ በርካታ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች እንደሚገኙ ጠቅሰው ቅርሶቹን ከመጎብኘት ባለፈ ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ ሰላም ወሳኝነት አለው ብለዋል። ቀጣይነት እና ተያያዥነት ያላቸው ተመሳሳይ መድረኮች እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመርሐ ግብሩ የቁንጅና ውድድር፣ ፉከራና ሽለላ እንዲሁም ሌሎች አዝናኝ እና አስተማሪ ዝግጅቶች ቀርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!