
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ክሌጅ ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ እና የክህሎት ሥልጠና እየሠጠ ነው። የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ ዓለሙ እንዳሉት በቢሮው ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራ አንዱ ነው።
የሥራ ዕድል ፈጠራው ደግሞ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መሠረት ያደረገ እንዲኾን፣ ታይተው በሚጠፉ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሳይኾን ቀጣይነት ባላቸው ዘርፎች እና የቤተሠብን ሃብት በአግባቡ መጠቀም ላይ ያተኮረ መኾኑን ገልጸዋል። ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል።
እስከ አሁን 265 ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ከዚህ ውስጥ የሥራ ዕድል እና የክህሎት ሥልጠና የወሰዱት ከ165 ሺህ አይበልጡም። ወጣቶች የሥራ ዕድል እና የክህሎት ሥልጠና አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በክልሉ ከታኅሣሥ 8/2017 እስከ ታኅሣሥ15/2017 ዓ.ም የሚቆይ የሥራ ሥልጠና ንቅናቄ ሳምንት ተጀምራል። በዚህም 178 ሺህ ዜጎችን በማሠልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በከተሞች ኩታ ገጠምን መሠረት ያደረጉ የመሥሪያ ሸዶች እየተገነቡ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ በክልሉ የሚገኙ እንደ ተፈጥሮ ሃብት፣ ሰብል፣ እንስሳት የመሳሰሉ ጸጋዎች የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው። ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት መመሪያ እየተዘጋጀ መኾኑንም ገልጸዋል። መመሪያው ለአቅመ ደካሞች፣ ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ የሚሠጥ ነው።
የሥራ ዕድል ፈጠራው የተሳካ እንዲኾን የልማት ድርጅቶች እና የመንግሥት ተቋማት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አሰሜ ብርሌ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ኩታ ገጠምን መሠረት ያደረገ የማድለብ፣ የወተት፣ የአምራች ዘርፍ በተለይም ደግሞ ብረታ ብረት እና ጣውላ የመሳሰሉ ዕድገት ተኮር ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በዚህ ዓመትም በተለየ መንገድ ለመስሪያ እና መሸጫ ቦታዎች ግንባታ 50 ሚሊዮን ብር መመደቡን ነው የገለጹት። ከልማት ባንክ ጋር በመቀናጀት ሸዶችን ለመገንባት የሚያስችል ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል። ሠልጣኞችም በሥነ ልቦና ዝግጁ ኾነው ከራሳቸው ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከሠልጣኞች መካከል ራሄል ዳኘው የሚሠጠውን ሥልጠና መሠረት ያደረገ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መኾኗን ገልጻለች። በተለይም የመነሻ ካፒታል እና የመሥሪያ ቦታ መመቻቸት ከቻለ ከሚሰጠው ሥልጠና ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መኾኗን ነግራናለች።
ሌላኛው ሠልጣኝ አዱኛ እንዳለው መነሻ ካፒታል ለሌላቸው ወጣቶች ሥልጠናውን ከመስጠት ባለፈ ሌሎች ግብዓቶችን መደገፍ ቢቻል ውጤታማ መኾን እንደሚቻል ነው የገለጸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!