ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ አሠራርን በመከተል ሙስናን መታገል ይገባል፡፡

36

ገንዳ ውኃ: ታኅሳስ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ አሠራርን በመከተል ሙስናን መታገል እንደሚገባ የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ ገለጹ፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር በዓለም አቀፍ ለ21ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል የነገ ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ መልዕክት በተቋማት ሲሰጥ የቆየው የፀረ ሙስና ውይይት የማጠቃለያ መድረክ ተካሄዷል።

የውይይቱ ተሳታፊ መልካሙ ጫኔ ሙስናን እንዲፈጠር ያደረግነው ራሳችን ነን ብለዋል፡፡ ይህ ስግብግብነት ነው ያሉት ተሳታፊው ከብሉሹ አሠራር መራቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሌላኛው ተሳታፊ ሙሉዓለም ጌታሁን የሕዝብን ሃብት ስልጣንን መከታ አድርገው የሚሰርቁ አካላት ላይ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት ነው ያሉት፡፡

የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምግብ ፈንታ ሙስና አሁን ላይ እየጨመረ እና ለሕገ ወጥ መድኃኒት ዝውውር ምቹ እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጋሻው አራጋው ሕጋዊ ኾኖ ከመጣ ባለጉዳይ ይልቅ ሕገወጥ ኾኖ የመጣ ጉዳዩን ተሎ አስፈጽሞ እየሄደ ነው ብለዋል፡፡ ይህን የሀገርን ኢኮኖሚ የሚሰባብር አካሄድ መግታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሙስና እንዲፈጸም ጥሩ ኹኔታዎችን የሚያመቻቹ ተገቢው ማስተካከያ እንዲወሰድባቸው ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ የሕዝብ ሃብት እንዳይመዘበር ሁሉም የገባውን ቃል በማክበር ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ነው ያሉት። የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት የማኅበረሰቡን የአገልግሎት አሠጣጥ ምቹ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ አሠራርን በመከተል ሙስናን መታገል እንደሚያስፈልም ተናግረዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ አዲስ ምዕራፍ እንደኾነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
Next articleበኦሮሚያ ክልል ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 320 ተወካዮች ተመረጡ።