ተስፋ ያለው የፍራፍሬ ልማት በደቡብ ወሎ

45

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምግብ ራስን መቻል የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ ነው። በምግብ ራስን ለመቻል እና የሥርዓተ ምግብ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የፍራፍሬ ልማት አንዱ ነው። የፍራፍሬ ልማት ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል፣ አምራቾች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ፣ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት እና የሥራ እድል የመፍጠር አቅም አለው፡፡ የፍራፍሬ ልማት ሥነ ምህዳርን የማስተካከል አቅም እንዳለውም በባለሙያዎች ይገልጻል።

በኢትዮጵያ ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት ከሰጡ ክልሎች ውስጥ የሲዳማ ክልል አንዱ ነው። የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬ እና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዳይሬክተር መስፍን ቃሮይ በክልሉ ከዓመታት በፊት የፍራፍሬ ልማት ከተለምዶ አሠራር ያለፈ እንዳልነበር አስታውሰዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠጠው ትኩረት የክልሉን የፍራፍሬ ልማት ወደ 27 ሺህ 617 ሄክታር ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ 971 ሄክታሩ ምርት የሚሰጥ ነው ብለዋል። በዚህ ዓመት 4 ሚሊዮን ኩንታል የፍራፍሬ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ከ42 በመቶውን ደግሞ የአቮካዶ ምርት ይሸፍናል ነው ያሉት።

በክልሉ ወደ ውጭ ከሚላከው የፍራፍሬ ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ በየዓመቱ እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል። በዓመት እስከ 700 ሺህ ብር ገቢ የሚያገኙ አርሶ አደሮችን እንዳሉም ተናግረዋል። በክልሉ ትኩረት ከተደረገባቸው ሥራዎች ውስጥ የኩታ ገጠም ልማት አንዱ ነው። የችግኝ ልማት ሌላኛው ትኩረት ሲኾን በየዓመቱም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የተዳቀሉ የአቮካዶ ችግኞች ይሰራጫሉ ነው ያሉት።

በምርት ስብሰባ ወቅት ይከሰት የነበረውን ችግር ለመፍታት በቴክኖሎጅ እንዲታገዝ ማድረጋቸውንም አመላክተዋል። የገበያ ችግሩን ለመፍታት ደግሞ ማኅበራት ከአርሶ አደሮች በመሰብሰብ ለፋብሪካዎች እንዲያቀርቡ እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት። ይህም ምርቱ ሳይበላሽ ለፋብሪካዎች እንዲደርስ አስችሏል ነው ያሉት። የቆዩ የአቮካዶ ዝርያዎችን በተሻሻሉ ዝርያዎች ከእስራኤል በማስመጣት የማስፋት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የአማራ ክልልም ለፍራፍሬ ልማት ተስማሚ የኾነ የአየር ንብረት ያለው ክልል መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል። ደቡብ ወሎ ዞን ደግሞ ለፍራፍሬ የተመቼ አካባቢ ነው። በዞኑ ከቆቦ ጊራና እስከ ሸዋሮቢት የሚገኘው ተፋሰስ የቆላ ፍራፍሬን ለማልማት ከሚያስችሉ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ነው። ባለፉት ዓመታት ለፍራፍሬ ልማት በተሰጠው ትኩረት 48 ሺህ የሚኾኑ አርሶ አደሮች ወደ ልማት እንዲገቡ ተደርጓል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በአርጎባ ወረዳ 03 ቀበሌ ነዋሪው ሙሐመድ አሊ አንዱ ናቸው።

አርሶ አደር ሙሐመድ ወደ ፍራፍሬ ልማት ከገቡ ዘጠኝ ዓመት አስቆጥረዋል። በሩብ ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ልማት እንደጀመሩ የገለጹት አርሶ አደሩ አሁን ላይ በማስፋት በሁለት ሄክታር መሬት ላይ እያለሙ ነው። ከዚህ በፊት ከሀርቡ፣ ከኮምቦልቻ እና ሌሎች አካባቢዎች የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በማምጣት ይጠቀሙ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደር ሙሐመድ አሁን ላይ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ እና ሀብሃብን በማልማት ከራሳቸው አልፎ ለአካባቢው ገበያ እያቀረቡ ይገኛል።

በዓመት ማንጎ ብቻ 40 ኩንታል ምርት ያገኛሉ። በዓመት በትንሹ ከ400 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ነው የገለጹት። ባገኙት ገቢ አርጎባ ላይ ቤት ገንብተዋል። በቀጣይ ትራክተር እና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም የፍራፍሬን ልማት በስፋት ለማምረት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። በአትክልት እና ፍራፍሬ ሽንኩርት፣ ካሮት፣ በርበሬ እና ሌሎች ቅጠላቅጠሎችን እያመረቱ መኾኑን ነግረውናል።

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ አትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አሳልፍ አሕመድ በዞኑ ሊታረስ ከሚችለው 432 ሺህ 346 ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ 7 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በፍራፍሬ ልማት የተሸፈነ ነው ብለዋል። በፍራፍሬ ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ 5 ሺህ 300 ሄክታሩ ምርት መስጠት የሚችል መኾኑን ገልጸዋል።

ወረባቡ፣ ተሁለደሬ እና ቃሉ ወረዳዎች በስፋት የሚመረትባቸው ናቸው። በ2016 ዓ.ም ብቻ ምርት መስጠት ከቻለው የፍራፍሬ ልማት 574 ሺህ 885 ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል። በዞኑ 48 ሺህ አርሶ አደሮች በፍራፍሬ ልማት እየተሳተፉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ተፋሰስን መሠረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በጓሮ፣ በኩታ ገጠም እና በተፋሰስ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በ2016 ዓ.ም ከተተከለው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ ውስጥ 667 ሺህ የሚኾነው የአርሶ አደሮችን ሥርዓተ ምግብ ለማሻሻል በጓሮ ዙሪያ የተተከለ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመት በ328 ችግኝ ጣብያዎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ800 ሺህ በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም ከ2 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መሸፈን የሚችል ነው፡፡ አብዛኛው ችግኝ እየተዘጋጀ የሚገኘው ደግሞ በማኅበራት እና በመንግሥት የችግኝ ጣብያዎች ነው ተብሏል።

ዞኑ ለአዲስ አበባ፣ አፋር እና ጅቡቲ ካለው ቅርበት አኳያ የተመረተውን የፍራፍሬ ምርት በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ ተመራጭ ያደርገዋል። በዞኑ የፍራፍሬ ልማት መስፋፋት ተከትሎ በኮምቦልቻ ከተማ ኢንዱስትሪዎች እየተቋቋሙ ነው። በዞኑ ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ነው ያሉት ቡድን መሪው አሁንም ግን የችግኝ ጥራት ችግር እና የፍራፍሬ በሽታ ፈታኝ እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በቂ የሰው ኃይል አለመሟላት እና በቂ በጀት አለመመደብ ደግሞ ሌላኛው ችግር መኾኑን ነው የተናገሩት።

የችግኝ ጥራትን ማስጠበቅ፣ በሽታን መቋቋም የሚችል ዝርያዎችን እና በሽታውን መቋቋም የሚችል መድኃኒት ማዘጋጀት እና ማቅረብ የምርምር ተቋማት ኀላፊነት ወስደው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በበጀት መደገፍ እና የሰው ኀይል መሟላት ደግሞ የመንግሥት ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል። ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን የሶላር ቴክኖሎጅ፣ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች እና የጸረ ተባይ መርጫ መሳሪያዎች ማቅረብ እንደሚገባ አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ10 ሺህ በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleየውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ አዲስ ምዕራፍ እንደኾነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡