
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት አምስት ወራት ከ10 ሺህ በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ አስታውቋል፡፡ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሥራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና በቀሪ ወራት የትኩረት ነጥቦች ላይ ተወያይቷል ።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኃላፊ ላቂያው አንዳርጌ በበጀት ዓመቱ ለ47 ሺህ 38 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ በአምስት ወራት ለ10 ሺህ 268 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዚያዊነት የሥራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በከተማዋ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 154 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ለ324 ኢንተር ፕራይዞች ብድር መሰጠቱን የገለጹት ኃላፊው 38 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ከጸደይ ባንክ ጋር በመተባበር ማስመለሳቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋ መኮንን የሥራ እድል ፈጠራ የሁሉም ሥራዎች ማጠንጠኛ ማዕከል ሊኾን ይገባዋል ብለዋል።
በቀጣይ ሁሉም ተቋማት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በመምሪያው ለሥራ ፈጣሪዎች የአቅም ግንባታ መስጠቱ፣ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ተደግፎ መሥራቱ እና ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለማከናወን እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የብድር ማስመለስን ማጠናከር፣ ብልሹ አሠራርን ማጋለጥ እና የኢንተር ፕራይዞችን ቅሬታ መፍታት በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኮምዩንኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የከተማ አሥተዳደሩ እና የክፍለ ከተማ የሥራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ምክር ቤት በየጊዜው ሥራውን እየገመገመ እንዲመራ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው የተባለው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!