“ሕዝቡ የደገፈው ሰላምን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

109

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ሰላማዊ ሰለፍ መካሄዱን ተናግረዋል። ሰለማዊ ሰልፉ ግጭት በቃን፣ የምንፈልገው ሰላምና ልማት ነው የሚል መልእክት የያዘ መኾኑን ገልጸዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ ሕዝባችን ምን ያክል ሰላም እንደሚሻ ያሰያበት ነው ብለዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ሰልፎች እንዳይካሄዱ ለማስፈራራት እና ለማሸበር የተደረገው ጥረትም አልተሳካም ነው ያሉት። ሕዝቡ ግን ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን በመተው ሰላምን እንደሚፈልግ በነቂስ ወጥቶ አሳይቷል ብለዋል።

ሰልፉ ጥያቄ አለኝ የሚል ኃይል ሁሉ ችግሮችን በውይይት ነው መፍታት የሚገባው የሚለውን የሚያሳስብ መኾኑንም አመላክተዋል። ሕዝብ ከጎናችን ነው እያለ መንግሥትን በኃይል እናስወግዳለን የሚለውን ኃይል ያጋለጠ መኾኑን ተናግረዋል።

ሰልፉ እንደ መንግሥት ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ መንግሥት ለሰላም ያደረገውን ጥረት በአደባባይ ወጥቶ የደገፈበት ነው ብለዋል። ዛሬ ሕዝቡ መንግሥትን ብቻ አይደለም የደገፈው፣ የደገፈው ሰላምን ነው ብለዋል። ሰላም ሲኾን ለመንግሥት ትልቅ ዓቅም መኾኑን ነው የተናገሩት።

ዛሬ የተደረገው የሰላም ሰልፍ በቀጣይ ለሚደረገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጉልበት የሚፈጥር ነው ብለዋል። በሕዝባችን ትልቅ ኩራት ተስምቶኛል፣ ምስጋናም እናቀርባለን ነው ያሉት። ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ላደረጉ የጸጥታ ኃይሎች ምስጋና አቅርበዋል።

የዛሬው ሰልፍ ወደፊት ለሚደረገው የሕግ ማስከበር እና የሰላም ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት። መንግሥት ሰላማዊ አማራጮችን ቀዳሚ የችግር መፍቻ አድርጎ እንደሚጠቀምም አስታውቀዋል። አውዳሚ ተግባርን አንመርጥም፣ የምንመርጠው ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣውን ሰላማዊ አማራጮችን ነው ብለዋል።

ችግሩ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሰላም አማራጮችን መፈለጋቸውን እና ማስቀመጣቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰላም አማራጭ ለይስሙላ የምናደርገው ሳይኾን አምነንበት እና አዋጭ መኾኑን ተረድተን የምናደርገው ነው ብለዋል።

የዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝብ ሰላማዊ አማራጮችን ብቻ እንደሚፈልግ ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል። በሰላማዊ አማራጮች የማይጠቀሙት ላይ የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት እንደሚገባ የተረጋገጠበት መኾኑን ነው የተናገሩት።

የክልሉ ሕዝብ በአንድነት ወጥቶ ባሳየው የሰላም ፍላጎት ኮርተናል፣ ምስጋናም ይገባዋል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከጦርነት ያተረፍነው ሞት እና ውድመት ነው” የወግዲ ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleከ10 ሺህ በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡