“ሕዝባችን የፅንፈኛን ድርጊትና ሃሳብ በአደባባይ ማውገዙን ከልብ እናመሠግናለን፤ የሰጠውን የሰላም ጥሪም ከልብ እናዳምጣለን፤ ዛሬም ለሰላም እና ስለሰላም እጆቻችንን እንዘረጋለን” አቶ ይርጋ ሲሳይ

54

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በአማራ ክልል ከተሞች የደረገውን ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በማስመልከት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው መልእክት አስተላልፈዋል። አቶ ይርጋ በመልእክታቸው በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ታጣቂ ኀይሎች እንዲቀበሉትና ችግሮችን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ላለፉት በርካታ ወራቶች አጥብቆ ሲጠይቅ ቆይቷል ብለዋል።

የመጪው ጊዜ የክልሉ ሁለንተናዊ አቅም ላይ ተጨማሪ ፈተና ከመሆን ውጪ የጽንፈኝነት ጉዞ ለማንም እና ለምንም እንደማይጠቅም፤ በትጥቅ፣ በጽንፈኝነት መንገድና በግጭት የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንደማያገኙ በውል የተረዳው አስተዋዩ የአማራ ክልል ሕዝብ ዛሬም የኔ ብቻ ሃሳብ ይደመጥ የሚልን ፅንፍ በረገጠ አስተሳሰብ ተመርኩዘው ነጠላ ፍላጎትን በነፍጥ ለመተግበር የጥፋት መንገድን የመረጡ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ፤ የአማራ ክልልን የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ከልቡ ጥሪ አቅርቧል ነው ያሉት።

ክልሉ በተሟላ ሁኔታ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ በተለይም የግጭትና የመጠፋፋት ምዕራፍ ተዘግቶ የሰላም፣ የውይይት እና የድርድር መንገድ እንዲኖር በማድረግ በኩል በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ያላሰለሰ ጥሪ አድርጓል ብለዋል።

በመሆኑም የሕዝብን የሰላም ጥሪ በማዳመጥ ለገቢራዊነቱ የማያመነታው ፓርቲያችን ብልጽግና እና መንግሥት ዛሬም አዋጪውን መንገድ በመምረጥ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት እንደሁልጊዜው ዝግጁ ነው ብለዋል።

ለሰላምና ስለሰላም የትኛውንም አይነት መስዋእትነት መክፈል ይኖርብናል፤ ዓላማችንም ሰላምን ማምጣት ነውና። ክልሉን የልማት ማዕከል ማድረግ አለብን፣ ትምህርት ቤቶች መከፈት አለባቸው፡፡ ባልተገባ ሁኔታ በክልሉ ላይ እየደረሰ ያለው ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ መቆም አለበት ነው ያሉት።
ዛሬም የሕዝባችንን የሰላም ጥሪ ከልብ እናዳምጣለን፤ ለሰላም እና ስለሰላም እጆቻችንን እንዘረጋለን ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለአምስት ዓመታት የሚቆይ አካታች የዲጂታል ስትራቴጂ ሊተገብር መኾኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“ከጦርነት ያተረፍነው ሞት እና ውድመት ነው” የወግዲ ወረዳ ነዋሪዎች