
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (አይ ኤል ኦ) ጋር በጋራ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ላይ ያተኮረ ውይይት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እያካሄዱ ነው። ውይይቱ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች መነሻ በማድረግ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ድኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር) የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ከፖሊሲ የተሻገረ የዲጂታል አብዮትን ለማምጣት እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህም አካታች የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ተቀርጾ በሚቀጥሉት ወራት ወደ ትግበራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ስደተኞችን ያማከለ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሚኒስትር ድኤታው 35 በመቶ የሚኾነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢንተርኔት ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም ዶክተር ይይሽሩን ገልጸዋል። በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ፕሮግራም ማናጀር ስቴፈን ኦፒኦ ስደተኞችን በመቀበል ቀዳሚ ከኾኑት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መኾኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለዲጂታል ዘረፉ የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነውም ብለዋል።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ ኢትዮጵያ 35 በመቶ ለሚኾነው ሕዝቧ የኢንተርኔት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ መቻሏንም አንስተዋል። ይህም በኢትዮጵያ ስደተኞችን ያማከለ የዲጂታል ሥርዓትን ለመዘርጋት አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያመላክት መኾኑን ገልጸዋል።
መድረኩ ለአካታች የዲጂታል ስትራቴጂው ግብዓት ከተሠበሠበበት በኋላ በሚቀጥሉት ወራት ወደ ትግበራ የሚገባ ሲኾን ለአምስት ዓመታት ቆይታ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!