“የሕዝቡ ጥያቄ እና የመንግሥት ፍላጎት አንድ ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)

49

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። በስኬት የተጠናቀቀውን ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ አስመልክተው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ መልዕክት መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ እንደግፋለን፣ ክልላችንን የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ መንግሥት ሕግ በማስከበር የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ሊያስጠብቅ ይገባል፣ ጽንፈኛው ኀይል በጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈፅመው ግድያ፣ ማገት እና ማፈናቀል ሊቆም ይገባል፣ መከላከያ ሰራዊታችን፣ የፌዴራል እና የክልላችን የፀጥታ ኀይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን፣ ሰላማችንን እናፅና ልማታችንን እናስቀጥል የሚል ነው።

በሕዝባዊ ሰልፉ የተሳተፈው ሕዝብ በተለያዩ አካባቢዎች በጽንፈኛው ኀይል የተቀነባበሩ እና የከሸፉ የቦንብ ፍንዳታዎች እና የተኩስ እሩምታ ያልበገሩት ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ይህ የሕዝቡ ቁርጠኝነት እና የተላለፉት መልዕክቶች ጭብጥ የጽንፈኛው ኀይል፣ ባንዳ አክቲቪስቶች እና የደም ነጋዴ ሚዲያዎችን ያጋለጠ ኾኖ አልፏል ብለዋል።

“የሕዝቡ ጥያቄ እና የመንግሥት ፍላጎት አንድ ነው” ያሉት ዶክተር ለገሰ ቱሉ ይህም ሰላምን ማጽናት፣ በየትኛውም አካባቢ ላሉ ነፍጥ ያነገቡ አካላት የሰላም በር ክፍት ማድረግ፣ ልማትን ማስቀጠል እና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።

በመኾኑም መንግሥት የጀመረውን ሕግ የማስከበር፣ ሰላምን የማጽናት እና የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራ ሕዝቡን ባሳተፈ አግባብ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next articleለአምስት ዓመታት የሚቆይ አካታች የዲጂታል ስትራቴጂ ሊተገብር መኾኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።