“ሰላምን በትጋት ማጽናት የሰው ልጆች ሚና ነው” አቶ አሸተ ደምለው

38

ሁመራ፡ ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን “ግጭት እና ጦርነት በቃን! ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በሰቲት ሑመራ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰለፍ ተካሂዷል።

የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው፣ የርዕሰ መሥተዳድሩ አማካሪ ጥላሁን መኳንንት፣ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ወጣቶች በሰልፉ ተገኝተዋል።

የጊዜ ዑደት አያቋርጥም ቀን ቀንን እየተካ ዓመታትን ያበጃል፤ ዘመን ከዘመን ይሻገራል፣ በዚህ ዑደት ውስጥ የጨለመውን የማንጋ ሥራ የፈጣሪ ነው፤ “ሰላምን በትጋት ማጽናት ደግሞ የሰው ልጆች ሚና ነው” ያሉት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው። ሰላምን ለማጽናት ሁላችንም ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ጨለማን ለማስወገድ መብራት ከተጠቀምንበት፣ ጦርነትን በሰላም ከተካንበት፣ ትላንት የነበርንበትን፣ ዛሬ ያለንበትን ነገ የምንደርስበትን መርምሮ ወደ ጨለማው ዘመን ላለመመለስ ፣ብርሃናማውን ዘመን ለመግለጥ በተስፋ የተሞላ ዕይታ፣ በጥበብ የተሞላ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰማዕታትን አደራ በማክበር የወሰን እና የማንነት ጥያቄው በሕግ አግባብ ዕውን እንዲኾን ሰላምን በማስፈን፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ ከመንግሥት ጎን ልንቆም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ችግሮችን በውይይት መፍታት አስፈላጊ መኾኑን ያነሱት የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎቹ ላለፉት ዘመናት የሰላም እጦት እጅጉን ጎድቶናል ብለዋል። አሁንም ዳግም እርስ በርሳችን ደም ከመፍሰስ ወጥተን በአንድነት እና በመተባበር የተሻለች ኢትዮጵያን ልንገነባ ይገባል ብለዋል።

ሕዝቡ የማንነት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ እና የወደሙ መሠረተ ልማቶች ወደነበረ ቁመናቸው እንዲመለሱ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የውስጥ ሰላም እጦታችን ለውስጣዊ አንድነታችን እንቅፍት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ለዓመታት በግፍ እና በጭቆና ቀንበር ውስጥ ኾኖ ለማንነቱ እና ለነጻነቱ ሲታገል ቆይቷል፤ ይህንንም ለማጽናት ሰላማችን ልናስከብር ይገባል ብለዋል።

ተማሪዎች በሰልፉ ተገኝተው ትምህርታችን በነፃነት እና በትጋት ለመከታተል ሰላም ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል። ሰላምን በማስፈን የታጠቁ ኃይሎች የመንግሥት የሰላም ጥሪን በመቀበል ወደ ሰላም ሊመጡ ይገባል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦት ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ የመካነ ሰላም ከተማ እና የቦረና ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባንጃ ወረዳ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ የሚደግፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።