
ደሴ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን የመካነ ሰላም ከተማ እና የቦረና ወረዳ ነዋሪዎች በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ችግር የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ በመደገፍ በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
ታጥቀው የሚቀሳቀሱ አካላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እጃቸውን ለሰላም ሊዘረጉ ይገባል ብለዋል። በክልሉ የተከሰተው የሰላም ችግር በውይይት እና በድርድር ሊፈታ ይገባል ሲሉ የጠየቁት የሰልፉ ተሳታፊዎች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላኩ አያሌው ክልሉ የሰሜኑ ጦርነት ከፈጠረው ቀውስ ሳያገግም ጽንፈኛ ኀይሉ በአክራሪ ብሔርተኝነት የፈጠረው የሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ችግር ማስከተሉን ተናግረዋል፡፡ ጽንፈኛ ኀይሉ የአማራን ሕዝብ ከነበረበት ከፍታ ዝቅ ለማድረግ እየሠራ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት የተረጋጋ ሰላም ሲኖር እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡ ኅብረተሰቡም የሰላምን አስፈላጊነት እና የጦረነትን አስከፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሰላም ግንባታ ሥራው ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል።
የቦረና ወረዳ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ ብርሀኑ በዜ ሰላም በውይይት እና በመደማመጥ የሚጸና የሁልጊዜ ተግባር መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የሰላም እጦት ችግር የዛሬን ብቻ ሳይኾን የነገ ተስፋን የሚያሳጣ ነው ብለዋል።
ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ ኀይሎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡
ሁሉም አካል ለሰላም ዘብ በመቆም የአካባቢውን ሰላም እና ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሰልፉ ላይ የቦረና ወረዳ እና የመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!