
ደብረ ማርቆስ:ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ ከተሞች የተካሔዱ የድጋፍ ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸው ተገልጿል።
በክልሉ የተፈጠረው ችግር በሕዝቡ ላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩ ባሻገር የሰብዓዊ ጉዳትንም አስከትሏል። ይህን የሚያወግዝ እና ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቅ ሰልፍ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች እና የከተማ አሥተዳደሮች ተካሂዷል።
በሰልፉ አንድ ዓመት በተሻገረው የጸጥታ ችግር መምህራን ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ አልቻሉም፤ ሕጻናት የመማር መብታቸው ተገድቧል፤ ክልሉ ሠላም እንጂ ጦርነት አያስፈልገውም የሚሉ እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ሊወገዙ ይገባል የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ “ሕዝቡ ሰላምን አጥብቆ የሚሻ በመኾኑ መልዕክቱን በአደባባይ ለዓለም አሳውቋል” ብለዋል። የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በዞኑ ከ20 በላይ በሚገኙ ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች የተካሄዱ ሲኾን ሕዝቡ ድምጹን በአደባባይ እንዳይገልጽ ጸጥታውን የማስተጓጎል ሙከራዎችም ተደርገው ማክሸፍ እንደተቻለ አቶ ኑርልኝ ገልጸዋል።
ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ በተካሔደባቸው ወረዳዎች እና የከተማ አሥተዳደሮችም በሰላም መጠናቀቁን አሥተዳደሩ አስታውቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!