የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ፣ ጽንፈኝነትን በመቃወም ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኛነት በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።

18

ሰቆጣ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰልፈኞቹም የተለያየ መልዕክት ያላቸው መፈክሮችን አሰምተዋል።

መፈክሮቹም “ለአማራ ሕዝብ ሰላም እንጂ ጦርነት አይገባውም፤ ታሪካችንን ማስቀጠል እንጂ እርስ በርስ እየተገዳደልን ታሪክ አናበላሽ፤ መንግሥት ሰላማችንን ሊጠብቅ ይገባል፤ እኛ ከሰላም ጎን ነን፣ እኛ ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ነን” የሚሉ መልዕክቶች ተስተናግደዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ የተገኙት የሰቆጣ ከተማ የሃይማኖት አባቶች የሰላም ፎረም ምክትል ሰብሳቢ ሃጂ ሰሎሞን መሐመድ “አባቶቻችን የውጭን ጠላት በጋራ መክተው ያጸኗትን ሀገር እኛ እርስ በርስ ተባልተን ልናፈርሳት አይገባም” ብለዋል።

የታጠቁ ኀይሎችም ነፍጥ ለማንም እንደማይበጅ በመረዳት ወደ ሰላም ወዳዱ ሕዝባችሁ ልትቀላቀሉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሠቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ሰላምን እና ልማትን አብዝተው ለተጠሙት የክልላችን ሕዝቦች ስትሉ ከትጥቅ ትግል ወጥታችሁ በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ይገባል ሲሉ ለታጠቁ ኃይሎች ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ መቀበል ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አይደለም ያሉት ከንቲባው ሕዝቡ በሰልፍ ወጥቶ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉም አሳስበዋል።

በዋግ ኽምራ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ከ250 በላይ የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ተመልሰው የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ መኾኑን ያወሱት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊው ሹመት ጥላሁን ናቸው።

ለሰላም አሁንም ጊዜው አልመሸም ያሉት አቶ ሹመት የክልሉ ሕዝብ ያሉትን ጥያቄዎች በሰላም ጠይቆ መልስ እንዲያገኝ የሕዝባችሁን የሰላም ጥሪ ልትቀበሉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ሰላማችንን በማጽናት ልማታችንን እናስቀጥላለን” በሚል መሪ መልዕክት የተካሄደው የሠቆጣ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም ተጠናቋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporatio

Previous articleበአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ ተጠናቀቀ።
Next article“በመንግሥት በኩል ለሰላም፣ ለውይይት እና ድርድር የምትጠልቅ ጀምበር እንደሌለችም ደጋግመን ማረጋገጥ እንወዳለን” አቶ አደም ፋራህ