
ባሕር ዳር:- ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ሕዝባዊ የሰላም ሰልፍ ተካሂዷል።
በሕዝባዊ የሰላም ሰልፉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ እዮብ አግማስን ጨምሮ የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስፋው አዱኛ፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሰላም ሰልፍ ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
በሰልፉ መጨረሻ ንግግር ያደረጉት የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ አስፋው አዱኛ በአሁኑ ሰዓት በክልላችን እየተካሔደ ያለው ጦርነት መቆም እንዳለበት እና ይህ አላስፈላጊ ግጭትም አማራን ከነበረው ትልቅ ክብር ዝቅ ያደረገ ትግል ነው ብለዋል። ታጥቀው የወጡ ኀይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀበለው ስለሰላም ቆም ብለው እንዲያስቡ አሳስበዋል። የአማራ ሕዝብን ስቃይ ማራዘሙ ተገቢ እንዳልኾነም አስረድተዋል።
በሰልፉ የተገኙት የወረዳው ቤተ ክህነት ኀላፊ የካህናት አለቃ መልዓከ ሰላም ጌታሰው በላይ “ወንድም ከወንድሙ ጋር መገዳደል ይብቃን! ሁላችንም ለሰላም ዘብ ቁመን ሀገራችን ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ የተገኙት ነዋሪዎች ለክልላችን የሚያስፈልገው ሰላም እና ልማት ነው! ሰላም የጋራ ሃብት ነው! “ክልላችን የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን!” መከላከያ ሠራዊታችን እና የክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን! መንግሥት ሕግ በማስከበር የንጹሐን ገዳዮችን ለሕግ ያቅርብልን የሚሉትን እና መሰል መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ከማለዳ ጀምሮ የተካሄደው የሰላም የድጋፍ ሰልፍ ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ ተከናውኗል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!