“ጥሪያችንን ስሙን እና ሰላምን ምረጡ” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

44

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል። በሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። “ጦርነት ይብቃ ሰላምን እንሻለን” ያሉ ነዋሪዎች ለክልላችን የሚያስፈልገው ጦርነት ሳይኾን ሰላም እና ልማት ነው ብለዋል። መንግሥት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን ርምጃዎች እና በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

ክልሉ የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለንም ብለዋል። ጽንፈኛው ኃይል በንጹሐን ላይ የሚፈጽመው ግድያ፣ ማገት እና ማፈናቀል እንዲቆምም ጠይቀዋል። ጽንፈኞች እና ተላላኪዎች ከባዕዳን ተልዕኮ ወጥተው የሰላምን አማራጭ ሊከተሉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ንጹሐንን በግፍ እየገደሉ በአስከሬናቸው መነገድ አረመኔያዊነት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ግጭት ይበቃናል ነው ያሉት።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሰልፉ ተሳታፊዎች ሰላም ለሁላችን ያስፈልገናል ብለዋል። በሰላም እጦት ምክንያት ደሃ ሠርቶ እንዳይበላ ኾኗል ነው ያሉት። ሁሉም ተስማምተው በሰላም መኖር አለባቸው፣ ለእኛም ሰላም መስጠት አለባቸው ብለዋል። ሰላም እንዲሰጧቸውም ጠይቀዋል።

ሰላምን እንፈልጋለን፣ በሰላም እጦት ምክንያት ዋጋ ከፍለናል፣ ጉልበት አለኝ ያለ ሁሉ ነፍጥ ማንሳት የለበትም ነው ያሉት። በግጭቱ ውስጥ ያሉ ኃይሎች ወደ ሰላም መግባት አለባቸው ብለዋል። የሚያዋጣው ሰላም ብቻ መኾኑንም ተናግረዋል።

ጦርነት ለማንም እንደማይበጅ በግጭት ውስጥ በቆየንባቸው ጊዜያት ተገንዘበናልም ብለዋል። ዛሬ ያደረጉት ሰልፍ ጦርነት እንደበቃቸው ለማሳየት መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ከዚህ በላይ ማቆየት የክልሉን ሕዝብ ወደ መከራ መግፋት መኾኑንም ገልጸዋል ።

በሰላም እና በፍቅር ሁሉም አሸናፊ ይኾናል ነው ያሉት። በጦርነት አሸናፊ እንደሌለ እና ሁሉም ተጎጂ እንደሚኾን ገልጸዋል። ቁጭ ብሎ በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም ብለዋል። ጥሪያችን ስሙን እና ሰላምን ምረጡ ነው ያሉት። ለሰላም እጅ መስጠት ሽንፈት አይደለም ጀግንነት እንጂ ብለዋል።

የሕዝብን ስቃይ ተረድታችሁ የተከፈተውን የሰላም በር ተጠቀሙ ነው ያሉት። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ልጆቻችን እየተማሩ፣ ነጋዴዎች እየነገዱ፣ ገበሬዎች እያረሱ አይደለም ብለዋል። በጫካ የሚገኙ ወገኖች የሕዝብን ጥያቄ እና የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።

በውጭ የሚኖሩ ወገኖች በጦርነት እየከፈልነው ያለውን ዋጋ እያወቁት አይደለም፣ ስቃያችንን እያራዘሙት ነው ብለዋል። ጥያቄዎቻችን በሰላም ፈትተን ወደ ልማት መዞር አለብን ነው ያሉት። የእኛ ፍላጎት በሰላም ወጥቶ መግባት ነው፣ ጦርነት ሰልችቶናል ብለዋል። ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል ሁሉ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባውም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማንኛውም ችግር በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ተናገሩ።
Next article“ክልላችን የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቆማለን” የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ነዋሪዎች።