
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ማንኛውም ችግር በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ተናግረዋል። መንግሥት በተደጋጋሚ እያቀረበው የሚገኘውን የሰላም ጥሪ የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል::
በሰላማዊ ሰልፉ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች መንግሥት ሰላምን ለማስፈን እየተከተላቸው ያሉ የሰላም ጥረቶችን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተፈጠረው ቀውስ ለኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች መዳረጋቸውንና ያገኙት ትርፍ አለመኖሩን ተናግረዋል። ሰላም እንዲረጋገጥ ለተግባራዊነቱ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል ነዉ ያሉት።
ጦርነት ለ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አይመጥንም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕዝባችን የሰላም ጥሪ ለማድረግ በአንድነት ድምጹን በማሰማቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። ማንኛውም ችግር በሰላማዊ እና በውይይት ሊፈታ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
መንግሥትና ኅብረተሰቡ በጋራ ባደረጉት የሰላም ጥረት ደብረ ብርሃን ከተማ ከአንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም እየተሸጋገረች መኾኗንም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ለከተማው ልማትና መልካም አሥተዳደር መስፈን ከመንግሥት ጎን ቆሞ እያደረገው ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!