የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት ተጠናቅቆ ጥር 6/2017 ዓ.ም ይመረቃል።

62

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እድሳት ሲደረግለት የቆየው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የፊታችን ጥር 6/2017 ዓ.ም እንደሚመረቅ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሢራክ አድማሱ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አሥተዳዳሪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የቅድስ ሥላሴ ካቴድራል የእድሳት ሥራው ወደ መጠናቀቁ በመኾኑ የፊታችን ጥር 6/2017 ዓ.ም ታቦተ ሕጉ ወደ ነበረበት ቦታ ይመለሳል ተብሏል። የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በርካታ ቅርሶች፣ ውድ ዕቃዎች እና ሌሎች ቅርጻ ቅርጾችን በመያዝ ከአክሱም ጽዮን ቀጥሎ ሁለተኛው ታላቅ ሥፍራ ነው ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ የራሷን ጳጳስ መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የበዓለ ሲመት መፈጸሚያ፣ የተለያዩ ባለ ሥልጣናት እና ታላላቅ ሰዎች ህልፈት ዘላቂ ማረፊያ በመኾን ሲያገለግል ቆይቷል። ካቴድራሉ በርካታ ዘመናት ያለእድሳት በመቆየቱ ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረግ በሚል ወደ እድሳት ገብቷል ብለዋል ቆሞስ አባ ሲራክ።

172 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ቫርኔሮ ከተባለ ልምድ ያለው ተቋራጭ ጋር ውል ተወስዶ ዕድሳቱ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል። አሁን ላይ ሥራው 95 በመቶ መድረሱም ተነግሯል።

አጠቃላይ የእድሳት ሥራው የጥንታዊ እና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በስመ ጥር እና ልምድ ባላቸው ሙያተኞች ጥናት ላይ ተመሥርቶ መከናወኑን በሥራው የተሳተፉ አካላት ገልጸዋል ።

በተያያዘም በቀጣይ ታህሳስ 12/2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀንሮ በመላው ዓለም የቀጥታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች እና ሌሎች የምስጋና፣ የጉብኝት እና መሰል ዝግጅቶች በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ምዕመናን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

እድሳቱ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቅርብ ክትትል ሲደረግበት እንደነበረ የገለጹት ቆሞስ አባ ሲራክ የመገናኛ ብዙኅን እና ሌሎች በየደረጃው ያሉ ተቋማት፣ ግለሰቦች እንዲሁም ምዕመናን ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግስቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ በአማራ ክልል ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቅ ሰልፍ በመካሄድ ላይ ነው።
Next articleበከሚሴ ከተማ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ።