
ደሴ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ “ጦርነት ይብቃ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በከተማዋ የሚገኙ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተማሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ አሚኮ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በግጭቱ ምክንያት እየጠፋ ያለውን ሰብዓዊ ጉዳት እና የንብረት ውድመት በማውገዝ ስለሰላም ሊሰብኩ ይገባል ብለዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው በሰሜኑ ጦርነት ከተከፈለው ዋጋ በመማር ከግጭት አዙሪት በመውጣት ወደ ልማት መዞር ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት እና ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈቱም አሳስበዋል።
ጦርነቱ ከማንም በላይ አምራቹን ኀይል እየጎዳ እንደኾነ በሰላማዊ ሰልፉ የተሳተፉ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
ወጣቶች ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በሰልፉ ላይ የተገኙት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ያለሰለም ተማሪዎች መማር አይችሉም፣ ዜጎች ወጥተው ለመግባት ይቸገራሉ፣ ልማትም መሥራት አይቻልም ብለዋል።
በመኾኑም የሰላምን ዋጋ በመረዳት ሁሉም ዜጋ ለሰላም መስፈን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!