
ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ የሰላም ሰልፍ ተካሂዷል። በግጭቱ ምክንያት በርካታ ወገኖቻችንን አጥተናል፣ ለከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ተዳርገናል፣ ሰላም እንፈልጋለን ብለዋል የሕዝባዊ ሰልፉ ተሳታፊዎቹ።
ያለፈው ይብቃ፣ ከግጭት አዙሪት ልንወጣ ይገባል፣ ተንቀሳቅሰን መሥራት በሰላም ወጥተን መግባት እንፈልጋለን ያሉት ተሳታፊዎቹ ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ለወገኖቻቸው ሲሉ ፊታቸውን ወደ ሰላም ያዙሩ ብለዋል።
ሰላም ስለፈለግነው ብቻ የምናገኘው አይደለም፣ ሁላችንም ወደ ቀደመው ሰላማችን ለመመለስ ለሰላም እንተጋለን ነው ያሉት የሰልፉ ተሳታፊዎች።
በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ የሰላምን ዋጋ በመረዳት በሃሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገር ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል። ሁሉም ማኅበረሰብ የሰላም አምባሳደርነቱን በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል የሚል መልዕክትም አስተላፈዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለውም ለጋራ ሀገር በጋራ መትጋት እና ከገባንበት ችግር ፈጥነን በመውጣት የሕዝባችንን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ነፍጥ አንስተው በጫካ የሚገኙ ኀይሎችም መንግሥት በተደጋጋሚ ላቀረበው የሰላም ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ሕዝባቸውን ከከፋ ችግር መታደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሕዝባዊ የሰልፍ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የ602ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ሶፍያ መሀመድ በበኩላቸው ሰላም የጋራ ሃብት በመኾኑ ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሰላም እጦቱ ምክንያት ትምህርት፣ ጤና እና ሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎቶች በመስተጓጎላቸው ኅብረተሰቡ ለችግር እና ለእንግልት ተዳርጓል ያሉት ብርጋዴል ጄኔራል ሶፍያ መሀመድ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገር ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍ በሰላም ተጠናቅቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!