
ጎንደር: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ “ለሰላም ዘብ እንቆማለን” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር ሰላም በማጣቷ ዘርፈ ብዙ ችግር እየገጠማት መኾኑን አንስተው ንግድ እና ቱሪዝም ሰላምን አጥብቀው ይፈልጋሉ ብለዋል።
መንግሥት ሊፈታቸው የሚገቡ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠየቅ እና በነባር እሴት በመመካከር እና በሽምግልና ሥርዓት ችግርን ያለመስዋዕትነት መፍታት ይገባል ብለዋል።
የጎንደር የዘመናት የመልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት መደረጉን ያነሱት አቶ ቻላቸው የጎርጎራ ሪዞርት፣ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት፣ የኮሪደር ልማት እና ለዘመናት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
መንግሥት ለጎንደር ልማት የሰጠውን ትኩረት አድንቀው በከተማው ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ገናና ታሪክ ያላትን ጎንደር ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
በቀጣይ በጎንደር ከተማ በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው እንግዶች ለበዓሉ እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!