“አሚኮ የሕዝብን አንድነት በሚያጠናክሩ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው” ጃንጥራር ዓባይ

53

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ አዲስ አበባ አራት ኪሎ የሚገኘውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አዲሱን ስቱዲዮ ጎብኝተዋል። አሚኮ ከክልሉ አልፎ በአዲስ አበባ ቅርንጫፉን ከፍቶ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ እና ዲፕሎሚያሲያዊ ግንኙነትን የሚያጎለብቱ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኹነቶችን በመዘገብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባ ተናግረዋል።

አሚኮ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለአድማጭ ተመልካች ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባው አንስተዋል። አሚኮ ለሀገራዊ ለውጡ መሳካት ግንባር ቀደም በመኾን መሠረት የጣለ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ነው ብለዋል።

አሚኮ በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም የሀገርን መልካም ገጽታ ከፍ በሚያደርጉ እና የሕዝብን አንድነት በሚያጠናክሩ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመዘገብ ሚናውን እየተወጣ ያለ ተቋም እንደኾነም ጠቁመዋል።

ለሠላም መረጋገጥ፣ ለልማት፣ ለሕዝቦች አንድነት እና አብሮነት ማደግ እየተጋ ያለ ተቋም በመኾኑ እንደ ሀገር የሚያኮራ ትልቅ ሚዲያ ነው ብለዋል።

አሚኮ እንደ ሀገር አብሮነት እና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ ዘገባዎችን ከመሥራት ባሻገር ለአዲስ አበባ ልማት እና ዕድገት ግንባር ቀደም በመኾን የሚሠራቸው ዘገባዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል። ይህንም አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

አሚኮ በአዲስ አበባ ትልቅ ስቱዲዮ መገንባት መቻሉ በቀጣይ የተደማጭነት እና የተደራሽነት አድማሱን ከማስፋት ባሻገር በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭ እና ቀዳሚ ሚዲያ እንዲኾን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

አሚኮ ከዚህ የበለጠ ለመሥራት አቅሙን ማሳደግ እና ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር እያደረገ ያለውን የትብብር እና የቅንጅት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ያሰለጠናቸውን ሚሊሻዎች አስመረቀ።
Next articleኢጋድ ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶችን መከላከል ታሳቢ ያደረገ ሕገ-ደንብ ሊያጸድቅ ነው።